የዩናይትድ ስቴትሱ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር በኬኒያ የጤና እክል ገጠማቸው

አባይ ሚዲያ ዜና 

የአፍሪካ ይፋዊ ጉብኝታቸውን ከኢትዮጵያ የጀመሩት የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሬክስ ቲለርሰን የጤና እክል ገጥሟቸው እንደነበረ ተዘገበ።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ በኬኒያ ሲገኙ ለቅዳሜ የያዙትን ፕሮግራሞች በህመም ምክንያት ለመሰረዝ እንደተገደዱ ሪፖርቶች ያመለክታሉ። የህመማቸው መንስኤ ከስራ መደራረብ ጋር የተያያዘ እንደሆነ እና ወደ አፍሪካ ከማቅናታቸው በፊት በዩናይትድ  ስቴትስ በስራ ተወጥረው እንደነበሩ ለመረዳት ተችሏል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገናኝተው እንዲወያዩ በቀረበው እቅድ ላይ ተጠምደው መቆየታቸው ለውጭ ጉዳዩ የጤና መታወክ ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ተጠቁሟል።

ከኬኒያ በተጨማሪ ናይጄሪያ እና ቻድን የመጎብኘት እቅድ የያዙት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሬክስ ቲለርሰን የጤናቸው ሁኔታ እንደተሻሸለ እና በጉብኝታቸው የያዙትን ፕሮግራሞች  እንደሚያከናውኑ ተገልጿል።

ሬክስ ቲለርሰን፣ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው መንግስት ለህዝቡ የበለጠ ነጻነት እንዲሰጥ በመጠየቅ የአስቸኳይ ጌዜ አዋጁ በኢትዮጵያ ለሚታየው የፖለቲካ ቀውስ መፍትሄ ያመጣል ብላ አገራቸው ዩናይትድ ስቴትስ እንደማታምን የሚገልጽ ይዘት ያለው አስተያየት መስጠታቸው ይታወሳል።