አባይ ሚዲያ ዜና

በጀርመን ኑረንበርግ ከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያኖች የአድዋ 122ኛ ዓመት የድል በአልን በልዩ ልዩ ማራኪ  ፕሮግራሞች ሲያከብሩ ውለዋል። በአሉን ለማክበር አዳራሹን ሞልተው የተገኙ ታዳሚዎች በኢትዮጵያ በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸውን እያጡ ያሉትን ንፁኋን ዜጎቻችንን ለማሰብ የሕሊና ፀሎት አድርገዋል።

የነፃነት ተምሳሌት የሆነውን የአድዋ ድልን ለማሰብ በዚህች ከተማ የተዘጋጀውን ፕሮግራም በኃላፊነት በማቀናጀት እና በማስተባበር በተሳካ መልኩ እንዲከበር ያደረገው በጀርመን ኑረንበርግ ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያውያን ማህበር እንደሆነ የማኅበሩ ፀሐፊ ለአባይ ሚዲያ ገልጸዋል። በኑረንበርግ የኢትዮጵያውያን ማህበር ውስጥ በየጊዜው እየተሳተፉ የሚገኙ ወጣቶች ቁጥራቸው እየጨመረ እንደሆነ በማሳወቅ በአሉን ደማቅ እና ውብ እንዲሆንም የወጣቶቹ ተሳትፎ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ አስረድተዋል።

የባርነት ቀንበርን በግድ ሊጭን የመጣው ወራሪ ጠላትን በሁሉም አቅጣጫ የሚገኙ ኢትዮጵያውያኖች በመተባበር በአድዋ ላይ ድል እንዳደረጉት ያስታወሱት የማህበሩ ፀሐፊ፤ ዛሬም አገራችንን ካለችበት ውስብስብ ችግር ማዳን የምንችለው በሕብረት እና በአንድነት ቆርጠን ስንሰራ እንደሆነ የኢትዮጵያውያኖች ማህበር ፀሐፊ የሆኑት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። 

በጀርመን ኑረንበርግ  ከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያኖች የአፍሪካ ኩራት የተባለለትን የአድዋን በአል ለማሰብ አዘጋጅተው ያቀረቡት ፕሮግራም ከታዳሚው ከፍተኛ አድናቆትን ማግኘት ችሏል።  የጥቁር ኩራት የሆነውን የአድዋን ድልን ለማሰብ በአዳራሹ የተገኙት ኢትዮጵያውያኖች የነገው ተስፋ የሆኑት ህፃናት፣ በባህል አልባሳት አሸብርቀው፣ የልጅነት ዘመን ትዝታን በሚቀሰቅስ ጨዋታቸው እንዲሁም ተሰምቶ በማይጠገበው የልጅነት አንደበታቸው አባታቸውን ታሪክ ንገረን በማለት ከእግሩ ስር ተሰባስበው ሲጠይቁ የሚያሳየው ትእይንት በአሉን ለማክበር በአዳራሽ የተሰበሰቡትን ታዳሚዎች ቀልብ የሳበ ነበር።

ይህ የኢትዮጵያውያኖች ማህበር በዚህ ከተማ የተመሰረተው ዘርን፣ እምነትን ወይም ብሔርን ማዕከል አድርጎ ሳይሆን አንድነትን እና ኢትዮጵያዊነትን በማንገብ እንደሆነ ማህበሩ ውስጥ ለረዥም አመታት የቆዩ አባላት ለሚዲያችን ገልጸውልናል።  

በጀርመን ኑረንበርግ ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያውያኖች ማህበር በነዚህ የአመታት ጉዞ ውስጥ ታዋቂ ኢትዮጵያውያኖችን እንዲሁም ምሁሮችን ከኢትዮጵያ በመጋበዝ ከማህበሩ አባላት ጋር እንዲገናኙ በማድረግ የላቀ ስራ ሲያከናውን እንደቆየ እነዚሁ አንጋፋ የማህበሩ አባላት ለአባይ ሚዲያ ተናግረዋል።

የጥቁር ኩራት የተባለለትን የአድዋ ድልን የቀደሙ አባቶቻችን እንዲጎናጸፉ የረዳቸው በመካከላቸው የነበረው ፍቅር፣ እምነት እና አንድነት እንደሆነ በመጠቆም እርስ በእርስ መከፋፈላችን ለድል ሳይሆን ለጥቃት እንደሚያጋልጠን ከሚዲያችን ጋራ ቆይታ ያደረጉት የማህበሩ አባላት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።  ማህበሩ በጀርመን አገር ከሚገኙ ጠንካራ  የኢትዮጵያውያን ማህበር ውስጥ አንዱ እንደሆነ በመግለጽ  ከቅርብ ጊዜያት ጀምሮ በርካታ ተስጥኦ ያላቸው አገር ወዳድ ወጣቶች ማህበሩን በመቀላቀል አበረታታች ስራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙም አስተያየት ሰጪዎቹ አክለው ተናግረዋል። 

አንድነትን ሃይላቸው በማድረግ ለነፃነት ተዋድቀው አለምን ባስደነቀ መልኩ ድልን በአድዋ ላይ የተጎናፀፉ ውድ ኢትዮጵያውያኖችን በግጥሞችና በጥናታዊ ፅሁፎች በመዘከር ዛሬም አገራችን ዳግም አድዋን፣ ዳግም ድልን እንዲሁም የአድዋ ድል ሚስጥር የሆነውን አንድነትን ከየትኛውም ጊዜ በላይ እንደሚያስፈልጋት የሚያስረዱ መልዕክቶች ለማስተላለፍ ተሞክሯል። በአርበኝነት የተሰዉ፣ ህይወታቸው ተርፎ ክብርን የተጎናጸፉ አርበኞች እንዲሁም አርበኞችን በህክምና መስክ ሲያገለግሉ የነበሩ የአድዋ ጀግኖችም ስራቸው ሲወደስ በዚሁ ፕሮግራም ላይ ተደምጧል። 

በውጭ ወራሪ ጠላት ላይ የድል ታሪክን በአድዋ ያስመዘገበች ኢትዮጵያ አገራችን ዛሬ በተቃራኒው ወንድማማቾች የሚጋደሉባት እንዲሁም ልጆቿ ተስፋ ቆርጠውባት ጥለዋት በስደት የሚንከራተቱ መሆኗ የኋላ አኩሪ ታሪኳን ሙሉ በሙሉ እንዳያጠፋው ወጣቱ ትውልድ መንቃት እና መስራት እንዳለበት የሚያሳስቡ ግጥሞች እና ጥናታዊ ፅሁፎች በፕሮግራሙ ቀርበዋል። 

ለዚህ ቀን ያበቁንን አባት እና እናት አርበኞቻችንን እናስብ በሚል ርእስ የኢትዮጵያን ታሪክ በአጭሩ ለመተረክ የተሞከረ ሲሆን፤ በዚህ ፕሮግራም ላይ  በቀደምት ጊዜ የተለያዩ ታዋቂ የአለማችን ግለሰቦች ኢትዮጵያን እንዲሁም ኢትዮጵያውያኖችን እንዴት ሲገልጹ እንደነበረ መፅሃፍትን በማጣቀስ መረጃ ለታዳሚው ለማድረስ የተደረገው ጥረትም ቀልብን የሳበ ነበር።  

በአድዋ ድል ከፍተኛ ሚና በመጫወት ደማቅ ታሪክን ያስመዘገቡት እቴጌ ጣይቱን ለማሰብ የተዘጋጀውን ተውኔት በአዳራሹ የተገኙትን ታዳሚዎች አስደስቷል። እቴጌ ጣይቱ የውጫሌ ውል የሆነውን አንቀጽ 17ን በመቃወም ከጣሊያኑ ኮንትአንቶሎኒ ጋር ያደረጉት እልህ የተሞላበት እና ቆራጥ ንግግር የታዳሚዎችን ቀልብ በእጅጉ ለመሳብ ችሎ ነበር። የጣሊያኑ ኮንትአንቶሎኒን ኢትዮጵያ የውጫሌን ውል የማትፈርም ከሆነ ጦርነት እንደሚታወጅባት ለማስፈራራት ሲሞክር እቴጌ ጣይቱ ጀግንነት በተሞላ መልኩ የሰጡት ምላሽ ታዳሚውን አስደንቆ አዳራሹን በጭብጫባ አድምቆታል። የእቴጌ ጣይቱ ቆራጥነትን በመደገፍ የቤተ መንግስቱ ጠባቂዎች ያደረጉት ወኔ የተሞላበት ፉከራና ሽለላ ከተመልካቾቹ ከፍተኛ አድናቆት አግኝቷል። 

አድዋ ክብር ለአባቶቻችን በሚል ርእስ በአሉን ለማስታወስ በእለቱ ለታዳሚዎች የቀረበወ ዘጋቢ ፊልም ንጉሰ ነገስት አፄ ሚኒሊክ ለአድዋ ጦርነት ክተት ከማወጃቸው በፊት ብልሃት የሞላበት ዝግጅት ሲያደርጉ እንደነበረ አስቃኝቷል። በአንፃሩ የጣሊያን ወራሪ ኢትዮጵያውያንን ለማንበርከክ ሲያደርጉ የነበሩትን ወታደራዊ እና ስትራቴጂካዊ ዝግጅቶች ምን እንደሚመስል በዚሁ ፊልም ተካትቶ ለታዳሚዮቹ ቀርቧል። አፄ ሚኒሊክ ወራሪ ጠላትን ለማሸነፍ መላ ኢትዮጵያውያንን ለማዋሃድ እንደጣሩ እንዲሁም ለነፃነት ቁልፍ የሆነውን አንድነትን በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንዲሰርፅ ለማድረግ እንደጣሩ በዘጋቢው ፊልም ተተርኳል። ፊልሙ ከተጠናቀቀ በኋላ ቀደምት ኢትዮጵያውያን በስነ ጥበብም ሆነ በጀግንነት አኩሪ ታሪክን ማስመዝገብ ሲችሉ በአሁኑ ጊዜ ግን አገራችን በተቃራኒ መንገድ መሄዷ ምክንያቱ እና መፍትሄው ላይ ውይይት ተደርጓል። 

የአድዋ ድልን ለማስታወስ በተዘጋጀው በዚሁ ፕሮግራም ላይ ታዳጊ ህፃናት የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ተንበርክከው በመቀበል በዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ አገራዊ ዜማ ታጅበው በመድረክ ፊት ሰንደቅ አላማውን ከፍ አድርገው ሲያውለበልቡ ታዳሚው በጭብጨባ አድናቆቱን ገልፆላቸዋል። ክብር የሚገባቸው አባቶቻችን አገራችንን ከባርነት ጠብቀው በነፃነት እንዳስረከቡን በዚህ ዘመን ያለነው ኢትዮጵያውንም የመከፋፈል እና የጥላቻ ቁርሾን በማሽቀንጠር ለመጪው ትውልድ ነፃነትን፣ እኩልነትን፣ አንድነትን ከምንም በላይ ደግሞ ሰላማዊ አገር የማስረከብ ግዴታ እንዳለብን እነዚህ የነገ ተስፋ የሆኑት በየዋህነት እና በፍቅር የተሞሉት ህፃናት መልዕክታቸውን በትእይንታቸው ለማስተላለፍ ሞክረዋል።

122ኛውን የአድዋ ድል በአል ለማሰብ በጀርመን ኑረንበርግ ከተማ የተደረገውን ፕሮግራም በማዘጋጀት  የተዋጣ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ትእግስት የሚጠይቀውን የማስተባበር እና የማቀናጀት ኃላፊነትን ትህትና፣ ህብረት ፣ ፍቅር እንዲሁም ኢትዮጵያዊነትን በተሞላበት መንፈስ በተሳካ መልኩ የተወጡት የኑረንበርግ ኢትዮጵያ ማህበር አባላት አድናቆት ከምስጋና ጋራ ይገባቸዋል።