በሞያሌ የተፈፀመው ጭፍጨፋ ታቅዶ የተከናወነ እንደነበር የኦሮሚያ ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ገለጹ

አባይ ሚዲያ ዜና
አቤኔዘር አህመድ

በኦሮሚያ ክልል የፍትህ ቢሮ እና ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ ባለፈው ቅዳሜ ቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ የመከላከያ ሰራዊት በሰላማዊ ሕዝብ ላይ የፈፀመው ጥቃት ታቅዶ እና ተቀነባብሮ የተፈፀመ ወንጀል ነው ሲሉ ድርጊቱን አወገዙ።

በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ ሸዋ በር በሚባል አካባቢ የመንግስት ወታደሮች በነዋሪዎች ላይ ተኩስ ከፍተው ከ10 በላይ መግደላቸውና ከ12 በላይ ማቁሰላቸው ይታወሳል።

ግድያውን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ተወካይ ሌተናል ጀነራል ሐሰን ኢብራሂም በአገዛዙ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው በሰጡት መግለጫ “የተሳሳተ መረጃ በመያዝ የተፈጠረ ግጭት ነው” ሲሉ ነበር የገለፁት።

የኮምኒዩኬሽን ኃላፊው አቶ ታዬ ደንደአ በበኩላቸው መግለጫው “ሕዝብን የመስደብ ያህል ነው” በማለት አጣጥለውታል። እንደውም የመንግስት ወታደሮች ሰላማዊ ነዋሪዎችን አንበርክከው በጭካኔ መግደላቸውን ለማረጋገጥ መቻሉን የኮምኒዩኬሽን ኃላፊው ለዶች ቬሌ በሰጡት አስተያየት ገልፀዋል።

የሞያሌ ከተማ ነዋሪዎች የደህንነት ስጋት ስለአደረባቸው ወደ ጎረቤት አገር ኬኒያ በመሰደድ ላይ ናቸው። እስካሁን ከ50 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በመንግስት ወታደሮች የሚፈፀመውን ግድያ በመሸሽ ተሰደዋል። የኬንያ ቀይ መስቀል እርዳታ እያደረገላቸው እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።