ፕሬዝዳንት ትራምፕ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩን ሬክስ ቲለርሰንን ከስልጣን አባረሩ

አባይ ሚዲያ ዜና

ባልተጠበቀ መልኩ  ከሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን  ጋር በሶስት ወራት ውስጥ ለመወያየት የቀረበውን ጥያቄ የተቀበሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ የውጭ ጉዳይ ሚንስትራቸውን ሬክስ ቲለርሰንን ማባረራቸውን ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ስልጣኑንም ሲአይኤን (CIA) በዳይሬክተርነት ሲያገለግሉ ለቆዩት ለማይክ ፓምፔዮ እንደሰጡት ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሳውቀዋል።

ሬክስ ቴለርሰን በውጭ ጉዳይ ሚንስትር ስልጣናቸው በነበሩበት ወቅት ላደረጉት ስራዎች በማመስገን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከሬክስ ቲለርሰን ጋር ልዩነት እንደነበራቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ይፋ አውጥተዋል። ከሬክስ ቴለርሰን ጋር በሃሳብ ከማይስማሙበት ጉዳዮች መካከል ኢራንን በዋናነት እንደ ምሳሌ በመጥቀስ ከአዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ጋር ጥሩ ስራ እንደሚሰሩ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ለመወያየት ብዙ መሟላት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ሲጠቅሱ የቆዩት ሬክስ ቲለርሰን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከሰሜን ኮሪያው መሪ ጋር ለመወያየት መስማማታቸው ቅሬታ እንደጫረባቸው ሲነገር ቆይቷል።

ጂና ሃስፔል በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት የሲአይኤ (CIA) ዳርይሬክተር ሆነው እንዲያገልግሉ እንደተመረጡ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በመልክታቸው አሳውቀዋል።