አሸንዳ የትግራይ በዓል ብቻ መሆኑን ለማሳየት የተዘጋጀው ፕሮግራም ከሸፈ

አባይ ሚዲያ ዜና
አቢሰሎም ፍሰሃ

በ14/03/2018 እ.ኤ.አ ኖርዌይ በርገን ከተማ አሸንዳ በየዓመቱ በነሐሴ ወር ትግራይ ውስጥ ያሉ ልጃገረዶች እና ሴቶች ለሶስት ቀናት በነፃነት እንደሚያከብሩት እና ስለ ጥንታዊ የሴቶች ባህል ታሪክ ይናገራል በሚል ከትግራይ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመሆን በኖርዌጃውያኗ ቴራ ማያላንድ እና በቴዎድሮስ ሃይለሚካኤል የተዘጋጀው ዘጋቢ ፊልም ሳይታይ ፕሮግራሙ እንዲቋረጥ ተደረገ።

የፕሮግራሙ ዋና አላማ አሸንዳ የትግራይ ሴቶች ባህል ብቻ መሆኑን ለኖርዌይ ማህበረሰብ እንዲሁም ተጋባዥ ለነበሩ የበርገን ዩንቨርስቲ ፕሮፌሰሮች እና መምህራኖች ለማስተዋወቅ በተለይም ለዩኔስኮ ለማስመዝገብ የታቀደ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

በፕሮግራሙ ቅደም ተከተል መሰረት ዘጋቢው ፊልም ከታየ በኋላ የጥያቄና መልስ ፕሮግራም የተያዘ ቢሆንም ከፊልሙ በፊት ጥያቄ አለን በማለት በበርገን ነዋሪ የሆኑት አቶ ዳዊት እያዩ  እና አቶ ሚሊዮን ሽፈራው ድምጻቸውን ቢያሰሙም እድል ስላልተሰጣቸው በኣዳራሹ ውስጥ የነበሩት ኢትዮጵያውያኖች በሙሉ ከእየ አቅጣጫው የተቃውሞ ድምጽ በማሰማታቸው የተደናገጡት የፊልሙ አዘጋጆች ፖሊስ ጠርተው የሚቃወሙትን አስወጥተው መርሃግብሩን ለመቀጠል ቢሞክሩም ተቃውሞው በማየሉ ፖሊስ እንዲቋረጥ ወስኗል።

የፕሮግራሙን አላማ ቀድመው የተረዱት ኢትዮጵያውያኖች አሸንዳ የአንድ ክልል ባህል ብቻ እንዳልሆነ የሚገልጽ በራሪ ወረቀቶችን በማዘጋጀት ፊልሙን ለመመልከት በአዳራሽ ውስጥ ለነበረው ታዳሚ በማደልና በኢትዮጵያ መንግሰት ወታደሮች የተገደሉ የሴቶች እና ህጻናትን ፎቶ እንዲሁም መፈክሮችን በመያዝ መድረክ ላይ በመውጣት በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አስረድተዋል።