ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪዎች በሞት እንዲቀጡ ሃሳብ አቀረቡ

አባይ ሚዲያ ዜና

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአደንዛዥ ዕፅን ለመቆጣጠር በአዘዋዋሪዎች ላይ የሞት ቅጣት እንዲፈፀምባቸው ሃሳብ አቀረቡ።

በዩናይትድ ስቴትስ ለህመም ማስታገሻነትና ስቃይን ለመቀነስ የሚውሉ እጾች እንዲሁም በባለሙያ የሚታዘዙ ከሄሮይን ዕፅ የሚዘጋጁ መድኃኒቶች ሱስ እንደወረርሽኝ እየተዛመተ መሆኑ ይነገራል።

በዚህም የተነሳ ከ 2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሱሰኛ እንደሆኑ ሲታወቅ፣ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2016 ብቻ ከ 63 ሺህ በላይ ሰዎች በዚህ ሱስ  ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉ ታውቋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደራቸው የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ለመግታት ዝግጁ ቢሆንም የሞት ቅጣት ተግባራዊ ለማድረግ ግን ፍርድ ቤትና ፖለቲከኞች ተፅዕኖ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ገልፀዋል።

ሃገራቸው ዩናይትድ ስቴትስ በአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ላይ በሚወሰደው እርምጃ ቁርጠኛ ካልሆነች ጊዜ እየባከነ መሆኑን አስታውቀው ቁርጠኝነቱ የሞት ቅጣት ተፈፃሚ እስከሚሆን ድረስ መጓዝ እንዳለበት ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።