በኦሮሚያ እና በአማራ ከተሞች የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ ተነገረ

አባይ ሚዲያ ዜና
አቤነዘር አህመድ

በአማራና ኦሮሚያ ክልል የስልክ ኢንተርኔት አገልግሎት  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአወዛጋቢ ሁኔታ ከታወጀ ጊዜ ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ መቋረጡ ተገለጸ።   

መረጃ በፍጥነት ለማግኘት እንዲሁም ሐሳብን በነፃነት ለመግለጽ ህዝቡ ከሚጠቀምባቸው መሳሪያዎች አንዱ እና ዋናው ኢትንተርኔት እንደሆነ ቢታወቅም መንግስት በኢንተርኔት ላይ ከፍተኛ አፈና እያደረገ እንደሚገኝ ተነግሯል።

በኢትዮጵያ  ህዝባዊ እንቢተኝነቱን እና አገዛዙን በመቃወም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለመገደብ ይህ የኢንተርኔት አፈና ሆን ብሎ የተደረገ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል። 

ቄሮ፣ ፋኖ እንዲሁም ዘርማ በማህበራዊ ሚዲያዎች እና በኢንተርኔት በመታገዝ እየተናበቡ በአገዛዙ ላይ እያደረጉ ያሉትን የተቃውሞ እንቅስቃሴን ለማሽመድመድ የኢንተርኔት አፈናው እንደተፈለገ የኢንተርኔት ባለሙያዎች እየገለጹ ይገኛሉ።  

በመንግስት የፀጥታ አካላት የሚፈፀመውን ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ጥሰት ግድያና ድብደባ በአደባባይ ይፋ እንዳይደረግ የኢንተርኔት አቅርቦት ላይ አፈና እና እገዳ እየተደረገበት እንደሆነም ተንታኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የኢንተርኔት ተደራሽነት ያላትና በዚህ ላይ የኢንተርኔት ነፃነት የሌለባት አገር መሆኗን በዘርፉ ላይ ጥናት የሚያካሂዱ አለም አቀፍ ድርጅቶች ይገልፃሉ። 

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና የተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶች የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ የኢንተርኔት አገልግሎትን በመዝጋት ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመገደብ አፈናን እንደሚያባብስ በሚያወጧቸው መግለጫዎች ማሳወቃቸው ይታወሳል። 

ፍሪደም ሃውስ ዓለም አቀፍ ድርጅት በ2016 እና በ2017 የአለማት የኢንተርኔት ነፃነት ይፋ ባደረገበት ሪፖርት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት  የኢንተርኔት ነፃነትን በመገደብ የመጀመሪያው ደረጃ ላይ እንዳስቀመጣት ይታወቃል።