ሀብታም ነኛ፤ ከማንም በላይ ሀብታም ነኝ፤ የሰው ሃብታም

ተወዳጁ አርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም

እኔ በራሴ ጉዳይ ሰው ፊት መቅረብ ብዙም አይሆንልኝም፡፡ ፈተና ሲገጥመኝ የለመድኩት እመብርሀንን ከነልጇ ማስቸገር ነው፡፡ እሷም ማማለድዋን ልጇ መድሀኔ አለምም ፀሎቴን መስማቱን ለአንድም ቀን እምቢ ብለውኝ አያውቁም፤ ሁሌም ምላሻቸው ፈጣን ነበር፡፡ ታዲያ ግን አንድም ቀን ያገኘሁትን ባርኩልኝ እንጂ ሃብታም አድርጉኝ ብያቸው አላውቅም፡፡

ሀብታም ነኛ፤ ከማንም በላይ ሀብታም ነኝ፤ የሰው ሃብታም፡፡ ከዚህ በላይ ሀብት ከየት ሊገኝ!
ዛሬ የመጣሁት ላመሰግን ነው፡፡ ሁላችሁንም ላመሰግን፡፡
እናትና ልጁን በፊት ለፊታችሁ ላመሰግን!!

ውድ ባለቤቴን ጨምሮ ስለኔ መታመም ከኔ በላይ የታመሙትን ቤተሰቦቼን ላመሰግን!! ባንተ ህይወት ላይ አንተ የማዘዝ መብት የለህም ብለው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሰው ፊት ልመና የወጡትን ሃይሉ ከበደን፤ መቅደስ ጸጋዬን፤ ውድነህ ክፍሌን፤ ሳምሶን ብርሃኔን፤ መሰረት መብራቴን፤ ቴዎድሮስ ተስፋዬን እና ቴዎድሮስ ተሾመን ላመሰግን፤ ነው የመጣሁት፡፡ አዎ የመጣሁት እናንተን ቀን ከሌት ተሯሩጣችሁ የደረሰብኝ ፈተኛ እሰው ዘንድ እንዲደርስ ያደረጋችሁትን የሚዲያ ባለሙያዎችም ላመሰግን ነው፡፡ ግን ከሁሉም በላይ እንደገና የተወለድኩ ያህል እንዲሰማኝ ያደረገኝን የኢትዮጵያንያን ህዝብ እንዴት ብዬ እንደማመሰግን ቃላቶች አጠሩኝ።

ከሁሉም በላይ የናንተን ጥሪ ሰምቶ ከአለም ዳርቻዎች ሁሉ በአንድ ድምፅ የጠራኝን የኢትዮጵያን ህዝብ በምን ቁዋንቀዋ ላመስግነው፤ ፍቄ ያንተ መኖር ጥያቄ ውስጥ ከገባ አደለም አንዱን ሁለቱንም ኩላሊቴን ልቤንም ጨምረህ ውሰድና እኔ ሞቼ አንተ ኑር ያለኝን እኔን እና መኖር እንድጓጓ ያደረገኝን ከዚህ በፊት ከነመፈጠሩ እንኳን የማላውቀውን ኢትዮጵያዊ በበቂ ሁኔታ የማመሰግንበት ቋንቋ ከወዴት ልፈልግ፡፡

ከአሜሪካ፤ ከአውሮፓ፤ ከአረብ ሃገራት፤ ከኤሲያ፤ ከአውስትራሊያ ዘሬን ሳይጠይቁ ሀይማኖቴን ሳይመረምሩ ያላቸውንና ካላቸውም በላይ የለገሱኝንስ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የማመሰግንበትስ ቃል ከወዴት ላምጣ፡፡ ሶስት በሬዎች አሉኝ ሁለቱን ሸጬ እልክልሀለሁ እንጂ አንተማ በገንዘብ ችግር አትሞትም ብለው እኔን አድነው እሳቸው ግን ችግር ውስጥ ሊገቡ የተዘጋጁትን የኦሮሚያ ምስራቅ ሸዋ ሎሜ ወረዳ ገበሬንስ ለማመስገን ቃላቶች ይበቁ ይሆን እስር ቤት ሆነው የራሳቸው ጉዳይ ሳያስጨንቃቸው እኔ እያለሁማ አንተ አትቸገርም ብለው ከፍተኛ ገንዘብ የላኩልኝን አቶ ከተማ ከበደን ሆድ ይመርቅ ሁለታችንም ድነን ለመጨዋወት ያብቃን በሉልኝ፡፡

በዘጠና ሰባት አመታቸው በእግዚአብሄር እጅ ተይዘው ኩላሊት የሚሰጥ ከሆነ የኔን ኩላሊት ስጡት ብለው የላኩልኝን እማ ወርቅዬን ጨምሮ ለህይወታቸው ሳይሳሱ አካላቸውን ሊከፍሉልኝ የተዘጋጁትን ከሃምሳ በላይ ሰዎች የኢትዮጵያ አምላክ ያስባችሁ በሉልኝ፡፡

ፓውሎስ ሆስፒታልን እስካሁንም ላደረጉልኝ ወደፊትም ሊያደርጉ ቃል ለገቡልኝ አመስግኑልኝ፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ሊያሳክሙኝ ቃል በመግባታቸው እጅግ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ የኔን የህክምና ጉዳይ ባለሙያዎቹ እየመከሩበት ነው ግማሹ ውጭ ሃገር ሄደህ ብትታከም ይሻልሃል ይለኛል፤ ሌላው አይደለም እዚሁ ብትጨርስ ነው የሚሻልህ ይሉኛል፤ ከንቅለ ተከላውም በኋላ ያለው የህክምና ሂደትና ወጪም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡

ግን ከዚህ ሁሉ በፊት ያስጨነቀኝ አዲስ ጉዳይ ገጠመኝ፤

እኔ ስልሳው ላይ ነኝ፤ የቀሩኝ አመታት ከጣቶቼ ቁጥር አይበልጡም፤ እና ይህች ገና ነገዎቿ ተደርድረው የሚጠብቋት የ 18 አመት ቀንበጥ ሁለቱም ኩላሊቶቿ ደክመው በገንዘብ እጦት ስትሞት እያየሁ እኔ ቀድሜ ልታከም አልችልም፤
በዚህች አንድ ሳምንት ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ያስተማረኝ ፍቅርም ይህንን አያሳይም፡፡ በዚህ ምክንያት እኔ መሞት ካለብኝ ልሙት እንጂ እቺ ልጅ ሳትድን እኔን ቢላ አይነካኝም፡፡ እናም እንድኖር የምትፈልጉ ከሆነ መጀመሪያ እሷን አድኑልኝ፡፡ ለአሁን ያስፈልጋታል የተባለውን፤ ህዝብ ከሰጠኝ ላይ ቀንሼ እሰጣታለሁ፡፡ እስከመጨረሻው ድረስ ለኔ የመጣ በረከት ሁሉም ለሷም እንደሚደርስ ቃል እገባለሁ፡፡ ከሰጣችሁኝ ላይ ቀንሼ ይህን በማድረጌ ለድፍረቴ ይቅርታ እጠይቃለሁ፤ እንደማትከፉብኝ እና አለኝታነታችሁ እንደማይለየኝ ግን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

እንደኔ ታመው አስታዋሽ ያጡትን ሁሉ እኔ እንዳስባቸው እመብርሀን ከነልጇ ትርዳኝ፡፡

አመሰግናለሁ፡፡