በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ለኬኒያ መዘዝ ማምጣቱ አይቀሬ እንደሆነ ሒውማን ራይትስ ዎች ገለጸ

አባይ ሚዲያ ዜና

በሞያሌ የመንግስት ወታደሮች በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ በወሰዱት እርምጃ ምክንያት ወደ ጎረቤት አገር ኬኒያ የተሰደዱትን ኢትዮጵያኖች በማስመልከት የኬኒያ ባለስልጣናት  ዝምታውን መስበር እንዳለባቸው ሒውማን ራይትስ ዎች አሳሰበ።

በመንግስት ወታደሮች እርምጃ ንጽኋን የሞያሌ ነዋሪዎች ሲገደሉ፣ በርካታዎች ደግሞ ሲጎዱ ከ አስር ሺህ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያኖች መኖሪያቸውን ጥለው ወደ ኬኒያ መሰደዳቸው ይታወሳል።

በኢትዮጵያ ያለውን አገዛዝ በመቃወም የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በሚደረጉበት በዚህ ወቅት አገሪቷ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እንደምትገኝ የመብት ተከራካሪው ሒውማን ራይትስ ዎች በመግለጽ፤ በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ለኬኒያ መዘዝ ማምጣቱ አይቀሬ እንደሆነ በሞያሌ በመንግስት ወታደሮች የተደረገውን ግድያ በማስታወስ ሒውማን ራይትስ ዎች ኬኒያን አስጠንቅቋል። 

አገዛዙ በህዝቡ ላይ የሚወስደው የሃይል እርምጃ እየጨመረ ከመጣ እና በኢትዮጵያ የጸጥታ ሁኔታው ከተባባሰ ዜጎች ራሳቸውን ለማዳን ሲሉ ወደ ኬኒያ ሊያቀኑ እንደሚችሉ በቅርቡ በሞያሌ የተፈጸመውን ድርጊት እንደ ምሳሌ በመጥቀስ፤ ይህ የህዝብ ስደት ኬኒያን ላልተፈለገ ጫና ሊዳርጋት እንደሚችልም የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆነው ሒውማን ራይትስ ዎች ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት በአገሩቱ ዘለቀታዊ ሰላምን ሊያመጡ የሚችሉ ቁልፍ ማሻሻያዎችን እንዲያደርግ በምስራቅ አፍርቃ ከሚገኙ አገራት መካከል ኬኒያ ከፍተኛ ሚና መጫወት እንዳለባት ሒውማን ራይትስ ዎች በመግለጫው አስፍሯል።

ሚሊዮኖች አገዛዙን በመቃወም በኢትዮጵያ ለውጥ እንዲመጣ እንቅስቃሴዎች እያደረጉ እንደሆነ የጠቀሰው ሒውማን ራይትስ ዎች የኬኒያ ባለስጣናት ለምስራቅ አፍሪቃ ሰላም  እና ደህንነት ሲባል የኢትዮጵያን ወቅታዊ ችግር ለውይይት እንዲያቀርቡት ተጠይቋል።

የጸጥታ ሃይሎች በህዝቡ ላይ በሚወስዱት የኋይል እርምጃ ምክንያት በኢትዮጵያ ያለው ሰብአዊ ቀውስ ኬኒያን ጨምሮ የጎረቤት አገራት ድንበርን ሊሻገር እንደሚችል ሒውማን ራይትስ ዎች አስጠንቅቋል።