በአማራ ክልል ህጋዊ ፓርቲ ለማቋቋም የሚንቀሳቀሱ 19 ሰዎች ታሰሩ

አባይ ሚዲያ ዜና
አቢሰሎም ፍሰሃ

በአማራ ክልል ህጋዊ ፓርቲ ለማቋቋም የሚንቀሳቀሱ 19 ሰዎች በባህር ዳር ታስረው ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባቸው ታወቀ።

ምርጫ ቦርድ በሚፈቅደው መልኩ ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ ምስረታ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የነበሩት ግለሰቦች አዲስ አበባን ጨምሮ ከተለያየ የአማራ ክልል ከተሞች የተውጣጡ እንደሆነ የሚወጡት መረጃዎች ያሳያሉ።

ህገ መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ለመደራጀት ሲንቀሳቀሱ ተይዘው አሁን በእስር ላይ የሚገኙት ግለሰቦች በባህር ዳር የተገኙት ቅድመ ምስረታ ጉባኤ ለማድረግ ሲሆን ለእስር የተዳረጉት ውይይታቸውን አጠናቀው ለእራት በተሰባሰቡበት ጊዜ እንደሆነ ተገልፆዋል። እስረኞቹ በተያዙበት ወቅት ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል ተብሏል።

የሰብአዊ መብት ተሟጏቹ ጋሻው መርሻን ጨምሮ በተለያዩ ዩንቨርስቲ በመምህርነት የሚያገለግሉ ከታሳሪዎቹ መካከል እንደሚገኙ የታወቀ ሲሆን እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት የተወሰኑት የስም ዝርዝር ደርሶናል
1ኛ፣ አቶ ጋሻው መርሻ
2ኛ፣ የሱፍ ኢብራሂም (ወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበረና አሁን ጠበቃ)
3ኛ፣ ተመስገን ተሰማ (ወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር)
4ኛ፣ በለጠ ሞላ (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር)
5ኛ፣ አቶ ሲሳይ አልታሰብ
6ኛ፣ በለጠ ካሳ (የቀለም ቀንድ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረ)
7ኛ፣ ዳንኤል አበባው እና ንጋቱ አስረስ (የአማራ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ) ሲሆን አጠቃላይ ቁጥራቸው 19 መሆኑ ታውቋል።