እነ እስክንድር ነጋ በማይመች ሁኔታ ላይ እንዳሉ ተገለጸ

አባይ ሚዲያ ዜና
አቤነዘር አህመድ

ከመጋቢት 16 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በኮማንድ ፖስት ትዕዛዝ  በእስር ላይ የሚገኙት እነ እስክንድር ነጋ  በማያመች ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተነገረ።

አንዱአለም አራጌን ጨምሮ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ታስረው እንደሚገኙ እና ያሉበትም ሁኔታ የማያመች እንደሆነ ቤተሰቦቻቸው ለአሜሪካ ድምጽ ገልጸዋል። 

ከጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ  ቤት በፖሊስ  ተይዘው ለእስር በተዳረጉበት ቀናቶች ሰፋ ባለ ክፍልና ንፅህናው በተወሰነ መልኩ በተጠበቀ ክፍል ውስጥ እንዲቆዩ ቢደረጉም በአሁኑ ወቅት ግን በተጣበበና መፀዳጃ አጠገብ በሆነ ክፍል ውስጥ እንዲሆኑ መደረጉን የእስረኞቹ ቤተሰቦች አክለው ገልፀዋል።

በፖሊስ መምሪያው ውስጥ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ ያሉ በርካታ ሰዎች ቢገኙም በሚዲያ የሚታወቁት እስክንድር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ ፍቃዱ ማህተመወርቅ፣ አንዱዓለም አራጌ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣ በፍቃዱ ሃይሉ፣ ዘላለም ወርቅአገኘሁ፣ ወይንሸት ሞላ፣ ይድነቃቸው አዲስ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ተፈራ ተስፋዬና አዲሱ ጌታሁን ናቸው።

በኮማንድ ፖስቱ ያልተፈቀደ ስብሰባ አድርገዋል እንዲሁም በህግ የተከለከለ ሰንደቅ አላማ ተጠቅመዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸው ፖሊስ ምርመራውን አጣርቶ እንዳጠናቀቀና የኮማንድ ፖስቱን ትዕዛዝ እየጠበቀ መሆኑን አስታውቋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ  መመሪያ የሚከለክለውና ፍቃድ እንዲኖርም የሚያዘው በአደባባይ የሚደረጉ ሰልፎችና ስብሰባዎችን እንደሆነና እነ እስክንድር ነጋ ያደረጉት በየትኛውም መመዘኛ የአደባባይ ስብሰባ ወይም ሰልፍ ሊባል የሚችል እንዳልሆነ ይታወቃል።