በባህር ዳር ፖሊስ ጣቢያ እስረኞች እየተሰቃዩ እንደሆነ ታወቀ

አባይ ሚዲያ ዜና
አቢሰሎም ፍሰሃ

እ.ኤ.አ 26 ማርች 2018 ዓ.ም በምርጫ ቦርድ እውቅና ያለው ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት ከተለያዩ የሃገሪቷ አካባቢዎች የተሰበሰቡ 19 ምሁራን ባህር ዳር እራት ከሚበሉበት በፖሊስ ተይዘው መታሰራቸውን እንደዘገብን ይታወሳል።

የኢንስፔክተርነት ማዕርግ ያለው የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒፎርም በለበሠ ሰው ቀጥተኛ ትዕዛዝ ዛሬ ጠዋት ምግብ እንዳይገባ እና በዘመዶቻቸው እንዳይጠየቁ መከልከላቸው ተሰማ። በዚህም ምክነያት እጅግ በጣም ብዙ ርቀት ተጉዘዉ የመጡት ጠያቂዎች ከበር የተመለሱ ሲሆን በጠባቂ ፖሊሶች በር ላይ የደረሰባቸው መጉላላት ታሳሪዎቹን ክፉኛ እንዳሳዘናቸው ታወቀ።

ቀደም ሲል ከነበሩ ጠባቂዎች በተጨማሪ አዳዲስ የማይታወቁ ጠባቂዎች የተመደቡ ሲሆን ይህ ኢንስፔክተር የተለየ ትዕዛዝ የተሰጠውና ይህንኑ ለማስፈፀም የመጣ ስለመሆኑ አመላካች ነገሮች እንዳሉ እየተነገረ ነው።

በዚህ እስር ቤት በርካታ ወጣት ታሳሪዎች እንደሚገኙ ሲታወቅ ከነዚህም ወስጥ ከታሰሩ አንድ ወር ከ5 ቀን የሆናቸው የባህር ዳር እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ይገኛሉ። የታሰሩበትም ጉዳይ ‘ወያኔ ሌባ’ ብላቹሃል የሚል ሲሆን አስካሁን ድርስ የጠየቃቸው አካል እንደሌለ እና ፍርድ ቤትም እንዳልቀረቡ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ዜና በዚሁ እስር ቤት በባህር ዳር የገጠር ቀበሌ ሊቀመንበር በሆነ ግለሰብ ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞባቸው የታሰሩ ሁለት ግለሰቦች እንዳሉ ሲነገር፣ እነዚህ ግለሰቦች በሚያሳዝን ሁኔታ እጃቸው ታሰሮ ቶርች የተደርጉ እንደሆኑ ታውቋል።