ከናዝሬት መልካም ነገር ይወጣልን (በነጋ አባተ)

የናዝሬት ከተማ ከአይሁድ እምነት በተቃረነ መልኩ የሃጢአት ከተማ ናት ተብሎ በይሁድ ቀሳውስት ስለተፈረጀች ከዚያች ከተወገዘች ከተማ መልካም ነገር ይወጣል ተብሎ አይገመትም ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚያች ከተማ ተወለደ። እስከዛሬ ድረስ አይሁዶች ኢየሱስ ክርስቶስን ላለመቀበል ከሚያስቀምጧቸው ምክኒያቶች አንደኛው ከዚህች ከተማ መወለዱ ነው። አንዳንድ ጊዜ ካልተጠበቀ ቆሻሻ ስፍራ የሚያስደንቅ፤  እጅን በአፍ ላይ እንድንጭን የሚያደርግ መልካም ነገር ልናይ እንደምንችል አዕምሮአችንን ማዘጋጀት መልካም ነው።

የሰሞኑ የዶ/ር ዓቢይ ወደ ቁንጮው ስልጣን መምጣት  በመካከላችን ግራጫ መልክ ያለውን ምልከታ አያሳየ ነው መልካም ነው። የእይታ ልዬነቶች ይከበራሉ እንጅ አይጠሉም። አንዱም ህወሃት ኢሃዴግን ከምንቃወምበት መሰረታዊ እምነታችን  የሃሳብ ልዬነቶችን በሰለጠነ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ከጫካ አስተሳሰቡ ባለመውጣት በጠመንጃ ለመፍታት መሞከሩ ነው። እናም የሃሳብ ልዪነቶቻችንን አክብረን የምንፈታበት መንገድ ግን ጥበብንና መከባበርን የተሞላ እንዲሆን ያሻዋል ካለበለዚያማ ከዘመኑ አረመኔ ገዥዎቻችን በምን ተሻልን?።

ያለንበት እውነት የሚያስረዳን ህዝብ ፖለቲካውን በመሰሪነት ከያዙትና በእውነት ለህዝብ ነጻነት ከሚታገሉት ለመለየት የሚያስችለውን እውቀት ማዳበሩን  ፖለቲከኞቹ ሊረዱት ከሚችሉት በላይ  ሄዷል። ስለዚህ በህዝብ ልብ ውስጥ ለመገኘት ከእውነት ጋር ተስማምቶ መቆም ግድ ይላል ህዝብ ሌላ ፍላጎት/interest/ የለውም በእውነት የሚያገለግሉትን ብቻ ይፈልጋል እነዚያ ሰዎች ወደሚፈለገው ስፍራ እስኪመጡ ድረስም እየወደቀም እየተነሳም ትግሉን ይቀጥላል።

ዶ/ር ዓቢይ ከህወሃት ኢሃዴግ ጉያ መውጣቱ ተዓማኒነቱን ተፈታትኖታል። ይህ የሚያሳየን በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነትን ለማግኘት ምን ያክል ፈርሶ መሰራት እንደሚያስፈልገው ወለል አድረጎ የሚያሳይ ብርሃን ነው። ይህ በእውነት ለአንድ ሃገርን እመራለሁ ለሚል ድርጅት ትልቅ ኪሳራ ነው። በሌላ በኩል ግን በህወሃት ኢሃዴግ ውስጥ ከህሊናቸው ጋር የሚኖሩ ካንቀላፉበት የነቁ የሉም ብሎ ማሰብ ግን የማይፈወስ ጨለምተኝነት ይመስላል። የቀድሞዋን ሶቬዬት ህብረትን ስናይ እንደዚያ የአለት ያክል የደደረውን የኮሚኒስት ግንብ ከኮሚኒስቶች መሃከል ቡልቅ ብሎ እንደዚያ በ”ቀዝቃዛ ጦርነት” ስም የተወጠረውን የዓለም አየር እንዲረግብ ያደረገው በኮሚኒስት አስተሳሰብ ተቀርፆ ያደገው ጎርቫቾቭ ነው። ጎርቫቾቭ ፒሬስትሮይካ በሚል መጽሃፉ ይህች ሃገር ተሃድሶ ያስፈልጋታል በሚል የገማውን የሶቪዬትን አካሄድ ጎልጉሎ በማውጣት ህዝቡ አዲስ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲያራምድ እድል ከፍቷል።

እንደኔ እምነት ዶ/ር ዓቢይ በህዝብ ትግል የተወለደ ነው ባይ ነኝ። ይህንን በህዝብ ትግል የተቆጠረን ድል ተንከባብክቦ መያዝ ደግሞ የእያንዳንዳችን ሃላፊነት ነው ፖለቲካዊ ብልጠትም ነው። ወያኔ በዚህ ስዓት የሚጫወተው ቁማር ዓቢይን መልሰን ወደጉያው እንድንወረውርለት ነው። ምክኒያቱም ህወሃት በኢሃዴጋውያን መካከል በተፈጠረ መፈረካክስ  ያልተጠበቀ ውጤትን  ይዛ እንድትወጣ የተገደደችበትን ትዕይንት መቀየር ትፈልጋለች። ይህ ወጤት እንዲመዘገብ ደግሞ በአዞ ጥርስ መካከል ሆነው መስዋዕትነት ለመክፈል ያሳዪትን ቁርጠኝነትም ዋጋ ቢስ እንዳናደርግ ልንጠነቀቅ ያስፈልጋል። ዓቢይ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ እንዲችልና የበለጠ ድፍረትን እንዲላበስ ክንዱን በመደገፍ ከጎኑ ልንቆም ያስፈልገናል። ይህ ካልሆነና ነጻነት ፈላጊው ክፍል ከጎኑ ካልቆመ ማንን ይዞ ነው የህዝብን ጥያቄ  ለመመለስ የሚሰራው። ከዚያ ይልቅ ጅቦቹን ህወሃቶች በአስፈላጊው መንገድ ሁሉ እየተከላከልን የነጻነት ትግላችንን እንዲደግፍ ልንጠቀምበት ያስፈልጋል።  

እንጅማ እንደህወሃት ፍላጎትማ ቢሆን ኖሮ እንዳሻቸው የሚጋልቡትን ፈረስ ሃይለማርያም ደሳለኝን መቼም ቢሆን ማጣት አይፈልጉም ነበር። ጽሁፌን ሳጠቃልል ጨለምተኛ ሳንሆን የዓብይን መምጣት እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር ለመጠቀም ብንሞክርና በሌላ በኩል ደግሞ ከእንዝህላልነት ወጥተን ለበለጠ ትግል ራሳችንን የምናዘጋጅበትና ይበልጥ የምንታጠቅበት ጊዜ እንዲሆን ማድረግ ብልህነት ነው እላለሁ።