የጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ንግግር ተስፋንም ስጋትንም እንዳጫረ ተነገረ

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን

ቃለ መሃላ የፈጸሙት አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ ሰላምን እና ብልጽግናን ለማምጣት ድርጅታቸው ኢህአዴግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲሁም ከአገር ውጭ ካሉ ኢትዮጵያውያን ጋራ በመግባባት ለመስራት እንዳቀደ ተናገሩ።

ቀልብን የሳበ እና ከዘረኝነት ይልቅ ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ በተሰማበት ንግግራቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ ህዝቡ መንግስትን የመተቸት፣ የመቃወም እንዲሁም በነጻነት የመናገር መብቶቹ መጠበቅ እንዳለባቸው በመጠቆም መንግስትም መልካም ተግባራት እንዳከናወነ ሁሉ ደካማ የሆኑ ድርጊቶችን መፈጸሙንም አምነዋል። 

ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት እና ሉአላዊነት ህይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ አባቶቻችንን እና እናቶቻችንን  በታሪክ ወደ ኋላ ተጉዘው በማወደስ የኢትዮጵያውያን አንድነት እንዳይለያይ ተደርጎ የተገመደ እንደሆነ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ስንኖር ኢትዮጽያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን በማለት “አማራው በካራማራ፣ ትግሬው በመተማ፣ ኦሮሞው በዐድዋ፣ ሱማሌው፣ ከንባታው፣ ወላይታው፣ ሀድያው፣ ሀረሪው እና ሌሎችም በባድመ  ለአገራቸው ሞተው አፈር ሆነዋል” የሚል የአንድነትን መንፈስ የሚያንጸባርቅ ንግግር ሲያደርጉ ተደምጠዋል። 

ከውጭ አገር ጋር ያለውን ግንኙነትም ለማሻሻል እንደሚጥሩ የገለጹት ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከኤርትራ ጋር ያለውን ግጭትም በሰላማዊ እና በወንድማማችነት መንፈስ ለመፍታት እንደሚጥሩ ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ንግግር መሳጭ  እና ቁም ነገር ያዘለ እንደሆነ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ቢገልጹም የጠቅላይ ሚንስትሩ ተስፋ የተሞላበት ቃላት ግን በተግባር ሳይቀየር መክኖ እንዳይቀር ስጋታቸውን የሚገልጹም አስተያየት ሰጪዎች ተሰምተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ አገሪቷ ከገባችበት የፖለቲካ ቀውስ ለማውጣት ከቃላት የከበደ ፈታኝ ስራዎች ከፊታቸው ተደቅኖ እንደሚጠብቃቸው ተንታኞች ሲገልጹ፤ በይበልጥ የአገሩቱ ቁልፍ ዘርፎች የሆኑት መከላከያው እና ደህንነቱ ይታዘዝላቸዋል ብሎ ለመገመት እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነም ተጠቅሷል።

በአገሩቷ የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ማሳመን፣ ለእኩልነት እና ለፍትህ እንዲሁም ለዲሞክራሲ ሲሉ በየእስር ቤቶች መንግስት አስሮ የሚያሰቃያቸውን ኢትዮጵያኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ ማስደረግ እና በአገሪቱ ላይ ግፍ እና በደል ሲፈጽሙ የነበሩ ባለስልጣናትን ለህግ እንዲቀርቡ ማስደረግ እንዲሁም ሁለት አስርተ አመታት የቆየውን አገዛዝ እየተቃወሙ ያሉትን ኢትዮጵያውያንን ቀርቦ እና አቀራርቦ የእውነት ምክክር ማድረግ የጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ፈታኝ የቤት ስራዎች እንደሆኑ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች እየተገለጸ ይገኛል።

የኢህአዲግ ሊቀመንበርነትን እና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትርነትን መንበር ለመጨበጥ የተደረገው ትግል ከፍተኛ እንደነበረ ለኦሮሚያ ቴሌቭዥን የገለጹት የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት ክቡር ለማ መገርሳ ዶክተር አብይ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው በመሾማቸው የተሰማቸውን ደስታ በሚንስትሩ ጽህፈት ቤት ተገኝተው ሲገልጹ ታይተዋል።

ለዚህ ክብር እንደሚበቁ በርግጠኝነት ይነግሯቸው ለነበሩት እና ለዚህም ደረጃ ለመድረስ ከማንም በላይ ትልቅ ውለታ ለዋሉላቸው ወላጅ እናታቸው በጥኡም አገላለጽ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በህይወት የሌሉትን እናታቸውን ተክተው ድርሻቸውን እየተወጡ ለሚገኙት የትዳር አጋራቸው እና የሶስት ልጆቻቸው እናት እንዲሁም የአገሪቷ ቀዳማይ እመቤት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።