ከማዕከላዊ በባሰ ደረጃ እስረኞች በምርመራ ወቅት የሚሰቃዩበት እስር ቤት

አባይ ሚዲያ ዜና
በአሰግድ ታመነ

ዛሬ እነ ስዩም ተሾመን ለመጠየቅ የሄዱ እማኞች እንደገለፁት ማዕከላዊ  እስካሁን አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የአይን እማኞች እንደገለፁት ምግብ የሚያቀርቡላቸው የማዕከላዊ  ሰዎች መሆናቸውና መርማሪዎቹም እነሱ መሆናቸውን ጠቅሰው ማዕከላዊ  አልተዘጋም ወደ ከፋ ማሰቃያ ቦታ አሸጋገሩት እንጂ ብለዋል።

ከማዕከላዊ የተዘዋወሩት የህሊና እስረኞች አሁን ያሉበትን ቦታ ሲገልፁት ክፍላቸው ውስጥ ካሜራ መኖሩንና ተሰብስበዉ ሲነጋገሩ መርማሪዎች እንደሚመጡ ጠቅሰው በክፍላቸው ውስጥ ካሜራ በመኖሩ ምንም ደህንነት አይሰማንም ብለዋል።

ሰው ታመመ ብለን ስንጮህ ሳይደርሱልን፣ ካርታ ስንጫወት በደቂቃ ይመጣሉ ብለዋል።

‘000’ (ዜሮ ዜሮ ዜሮ) የሚባሉ 18 የማግለያ (solitary confinement) ክፍሎች መኖራቸውና ክፍሎቹ ተዘግተው የሚውሉ ሲሆን አሁን አራት እስረኞች እንዳሉበት ሰዎቹ በደረቅ ወንጀሎች (ፖለቲካ ነክ ያልሆኑ ክሶች) ተጠርጥረው የታሰሩ ሲሆን፣ ሦስተኛ ፎቅ ላይ ተወስደው እንደሚመረመሩ ምርመራውን በማሰቃየት (ቶርቸር) ለመፈፀም አርክቴክቸሩ የተመቻቸ መሆኑም ታውቃል።

እዚህ የታሰሩ ሰዎች ከቀኑ 6:00 ሰዐት እስከ 8:00 ድረስ ፀሐይ መሞቅ ይፈቀድላቸዋል። በዚያ ሰዐት እነ ሥዩም ተሾመ ስለሚቆለፍባቸው አያይዋቸውም። ሥዩም ምርመራውን ከጨረሰ በኋላ ያገኘው ኩምሳ (?) የተባለ በነፍስ ማጥፋት የተጠረጠረ የአምቦ ሰው ጥፍሮቹ መነቃቀላቸውን አይቷል። “በጥቅሉ ቶርቸር ቆሟል የሚል የተሳሳተ ግምት መወሰድ የለበትም” ብለዋል።

ሜክሲኮ አደባባይ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ህንፃ ስር 45 ክፍሎች ያሉት የምድር ውስጥ እስርቤት መኖሩን የኢሳት ምንጮች የገለፁ ሲሆን ባለ 9 ፎቅ የፌደራል ፖሊስ ህንፃ ስር አንድ ሜትር ከሃምሳ በሁለት ሜትር ተኩል በሆኑ 45 የምድር ውስጥ ጠባብ ክፍሎች የማሰቃያ እስርቤቶች ናቸው። በነዚህ ክፍሎች የሚታሰሩ ዜጎች ታፍነው የሚወሰዱ እና የት እንዳሉ የማይታወቅ የህሊና እስረኞች መሆናቸውም ተገልፃል።