ሳውዲ 2.2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መርከብ ግዢ ከስፔን ጋር ልታካሂድ እንደሆነ ተዘገበ

አባይ ሚዲያ ዜና 

ሳውዲ አረቢያ ከስፔን 2.2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መርከብ ግዢ ልታካሂድ እንደሆነ የስፔንን የመከላከያ ሚንስትር ዋቢ ያደረጉ ዘገባዎች ተሰምተዋል።

2.2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣውን የጦር መርከብ ግዢ ስምምነት የሚደረገው በስፔን ዋና ከተማ በማድሪድ እንደሆነም የሚወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ።

በስፔን መንግስት የሚተዳደረው የመርከብ አምራች ኩባንያ አምስት የጦር መርከቦችን ሰርቶ ለሳውዲ አረቢያ እንደሚያቀርብ መረጃዎች ይጠቁማሉ። 

የስፔን የጦር ሃይል በበኩሉ የሳውዲ የጦር ጓዶችን እንደሚያሰለጥን እንዲሁም የስፔን ተቋራጮች በንጉሳዊው የሳውዲ አረቢያ ግዛት የባህር ሃይሉን ግንባታ ተኮናትረው እንደሚገነቡት ዘግቧል።

አምንስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ ሌሎች የሰብአዊ እና የእርዳታ ድርጅቶች ይህን የስፔን እና የሳውዲ አረቢያን የጦር መርከብ ግዢ ስምምነት እያወገዙት ይገኛሉ።

የመብት ተከራካሪዎች ሳውዲ አረቢያ የሰብአዊ መብት ጥሰት ትፈጽማለች በማለት ክሳቸውን ቢያሰሙም የሳውዲ መንግስት ግን ክሱን እያስተባበለ ይገኛል።

የሳውዲው አልጋ ወራሽ ልኡል መሃመድ ቢን ሳልማን በስፔን እያደረጉ ባሉት ይፋዊ ጉብኝት  ከስፔን ንጉስ እና ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋራ ተገናኝተው ሲነጋገሩ ከስፔን የመከላከያ ሚንስትር ጋርም ውይይት ማድረጋቸውም ተዘግቧል።