በወልድያ እግር ኳስ ቡድን ላይ የተላለፈው ውሳኔ ፖለቲካዊ እንደሆነ ተነገረ

አባይ ሚዲያ ዜና
አቢሰሎም ፍሰሃ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በወልዲያ እና ፋሲል ከተማ ጨዋታ ዙርያ ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎች ዛሬ የአማራ ብዙሃን መገናኛ በፌስቡክ ገጹ ዘግቦታል።

ውሳኔ
1. ለፋሲል ከተማ ፎርፌ እንዲሰጥ (3 ነጥብ + 3ጎል)
2. በመሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታድየም ለአንድ አመት ጨዋታ እንዳይካሄድ
3. ቀሪ የሜዳው ጨዋታዎችን ከወልዲያ በ500 ኪ.ሜ ርቀት እንዲያደርግ
4. 250 ሺህ ብር ቅጣት
5. የዳኞች ህክምና ወጪ እንዲሸፍን
6. አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ (አንድ አመት እገዳ+20,000 ብር)
7. ብሩክ ቃልቦሬ (አንድ አመት እገዳ + 10,000 ብር)

ፌዴሬሽኑ ይህንን አይነት ውሳኔ የወሰድኩት በወልድያ ከነማ እና በፋሲል ከነማ መካከል በነበረው የእግር ኳስ ጨዋታ ላይ መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ሊፈፀም አንድ ደቂቃ ሲቀረው ለፋሲል ከነማ ቡድን ፍፁም ቅጣት ምት በመሰጠቱ የወልድያ ከተማ እግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ አቶ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ያለ ዋናው ዳኛ ፍቃድ ወደሜዳ ሮጠው በመግባት የመሃል ዳኛ የሆኑትን አቶ ለሚ ንጉሴን በማነቅ፣ በመገፍተር እንዲሁም ደጋፊዎችን ለአመፅ በማነሳሳት የዳኛውን ውሳኔ ለማስቀየር በመሞከራቸው እና የወልድያ ከተማ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች ሚያዚያ 05 ቀን 2010 ዓ.ም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ወደፊት በወልድያ ስታዲየም ብንጫወት በውድድሩ ላይ ለሚፈጠረው ውጤት በደጋፊው አደጋ ሊደርስብን የሚችል በመሆኑ መፍትሄ ይፈለግልን የሚል አቤቱታ ማቅረባቸውን ከግምት ወስጥ በማስገባት ነው ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ረብሻው ሆን ተብሎ በህወሐት ሴራ የተፈጠረ መሆኑን ውሳኔው ማረጋገጫ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎች በተለይ የአዲግራት እና መቀሌ ቡድኖች ለፈጽሟቸው ስፖርታዊ ጨዋነት ከአንድ ዓመት በላይ ውሳኔ ሳያገኙ በእንጥልጥል ባለበት ሁኔታ ወልድያ ላይ የተላለፈው ውሳኔ ፖለቲካዊ መሆኑን ይገልፃሉ።