የሱማሌ ክልል ልዩ ሃይል በሞያሌ ህዝብ ላይ ጥቃት ፈጸመ

አባይ ሚዲያ ዜና
አቢሰሎም ፍሰሃ

ከአዲስ አበባ በ790 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሞያሌ ከተማ ልዩ ሀይል እየተባለ በሚጠራው በሶማሌ ክልል ወታደር በተሰነዘረ የቦምብ ጥቃት 50 ሰውች ሲቆስሉ 3 ሰዎች መገደላቸውን የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር እና የክልሉ ደህንነት ቢሮ ሲያስታወቅ የሞያሌ ከተማ ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤትም ፍንዳታውን ዘግቧል።

በሌላ በኩል መቀመጫውን ኬንያ ያደረገ ማርሴብ ሬዲዮ ጣቢያ የሞያሌን ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ኩኑ አብዱባን ዋቢ በማድረግ ከስምንት በላይ ጉዳተኞችን መረከባቸውንና 4ቱ በጥይት ተመተው የቆሰሉ ሲሆኑ 4ቱ ደግሞ በቦንብ ፍንጥርጣሪ የተጎዱ መሆናቸውን አረጋግጠውልኛል ሲል ዘግቧል።

በሌላ በኩል ሁለት አስከሬን እና ከ 20 በላይ ቁስለኛ ወደ ፊላሳ እና ሌሎች የጤና ተቋማት ተወስደዋል ሲል የዓይን እማኝ ለሬዲዮ ጣቢያው ተናግሯል።

የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር እና የክልሉ ደህንነት ቢሮ ከኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ የሚቀበለውን የፌዴራል ሠራዊት የዜጎችን ደህንነት ባለመጠበቅ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል።

ቀደም ሲል በኢትዮ-ሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልል ድንበር ላይ ለ አንድ ወር ያህል በቆየ ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲሞቱ ከአንድ ሚሊዩን በላይ የሚሆኑ መፈናቀላቸው ይታወሳል።

በድንበር ከተማዋ ሞያሌ እ/ኤ/አ መጋቢት 10 ቀን 2018 አ/ም የኢትዮጲያ የጦር ሠራዊት አባላት ቢያንስ 13 ሰላማዊ ዜጎች ሲገድሉ ሌሎች ከ20 በላይ የሚሆኑ ማቁሰላቸውን እና ከ50ሺ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ ኬንያ መሰደዳቸው ይታወሳል።

በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በተመረጡ በ3ኛ ቀናቸው ወደ ኢትዮ-ሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጅጅጋ ተጉዘው በሁለቱ ክልሎች መካከል የተከሰተውን አለመግባባት እንደሚፈቱ ከኢትዮ-ሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንቶች ጋር በመሆን ቃል እንደገቡ ይታወቃል።