የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ኢትዮጵያን፣ ኤርትራንና ጅቡቲን ይጎበኛሉ

አባይ ሚዲያ ዜና 

የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን በኢትዮጵያ፣ በኤርትራ እና በጅቡቲ  የሚያደርጉትን ይፋዊ የስራ ጉብኝት መጀመራቸው ተገለጸ።

በአሜሪካው ተጠባባቂ የአፍሪቃ ጉዳይ ረዳት ውጪ ጉዳይ ሚንስትር በሆኑት በዶናልድ ያማሞቶ የሚመራው ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ጉብኝቱን ከኤርትራ አስመራ ጀምሯል። ዶናልድ ያማሞቶ ከኤርትራ መንግስት ጋራ  እና በአስመራ ከሚገኘው የኤምባሲው ባልደረቦች ጋር መወያየታቸውም ተዘግቧል።

ከምእራባውያኑ አልፎ በእስያም እንደ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ አገር እየታየች ያለችውን ጅቡቲንም ሚንስትር ዶናልድ ያማሞቶ እንደሚጎበኙ የወጣው መርሃ ግብር ያሳያል። በጅቡቲ ቆይታቸው በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እንዲሁም በፀጥታ ጉዳዮች ላይ የድጋፍ እና የትብብር ውይይቶች ያደርጋሉ ተብሏል።

በወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት ምክንያት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያላት ግንኙነት እየሻከረ የመጣው ዩናይትድ ስቴትስ በሚንስትር ዶናልድ ያማሞቶ ጉብኝት በኢትዮጵያ መደረግ ስላለባቸው ዲሞክራሲያዊ ማስተካከያዎች ላይ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል። በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉብኝት ሽብርተኝነትን የመዋጋት ጉዳይም ሌላኛው የመወያያ ርዕስ እንደሚሆን ተጠቁሟል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ቀውስ ውስብስብ እንደሆነ በመግለፅ እነዚህን ችግሮች ለማብረድ ዩናይትድ ስቴትስ በተቻለ መጠን ለመርዳት ፍቃደኛ እንደሆነች የአፍሪቃ ጉዳይ ረዳት ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ዶናልድ ያማሞቶ ከወር በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መናገራቸው ይታወሳል።