“ነብሮ አውቃለሁ ያኔም አስተውያለሁ አንድ የከበደ የከበረ አላማ እንዳለህ የተለየ ነገር ነበረህ አሁን በግልጥ ተረዳሁት” ከሻሎም ሻሎም

ባይ ሜድያ

ከሻሎም ሻሎም

በ1978 ዓም አጋማሽ አካባቢ በሽዎች የሚቆጠሩ ለግላጋ ወጣቶች ወንዶ ጢቃ በሚገኘው የአየር ወለድ ማሰልጠኛ ጣቢያ ግብተው ከሰለጠኑ ቦሃላ በኤርትራ ምድር ለግዳጅ ተሰማሩ።
እነዚህም አብዛኛው በአስራዎቹ እድሜ እና በሃያኦቹ መጀመርያ ላይ ያሉ ወጣቶች ነበሩ ከነዛ ውስጥ አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አካባቢ ተወልዶ ያደገው ገዘሃኝ ገብረመስቀል አንዱ ነበር።
ኤርትራ አስመራ በመቶ ሁለተኛው አየር ወለድ ክፍለ ጦር መምሪያ ውስጥ ነው ያኔ እኔ እና ነብሮ የተገናኘነው ጎዳይፍ የሚባለው ሰፈር አካባቢ የአየር ሃይሉን ተጠግቶ ባለው ጦር ሰፈር ውስጥ ሁለት በሁለት በሆነች ትንሽ ድንኳን ውስጥ እኔ እና ገዛሃኝ ነብሮ ለሁለት ዓመት ገደማ አብረን በዛች ድንኳን ውስጥ ኖረናል።
በራሱ መንገድ የሚያጠበጥብ እንደ ብዙዎቻችን በይሉንታና በጓደኛ የማይወሰድ ነብሮ አፈንጋጭ ባህሪ ነበረው አፈንጋጭ ስል እንደብዙቻችን በቀላሉ በሰው የማይነዳ በአላማ የሚኖር ወታደር ነው ለማለት ፈልጌ ነው።
በረፍት ግዚያችን ወደ አስመራ ከተማ ለመዝናናት ስንወጣ ብዙዎችችን እንደምናደርገው ገንዘቡን ባልባሌ ነገር የማይበትን በመጠጥና በሴቶች የማያጠፋ መጥፎ ባህሪ የማይታይበት ሰው ነው።
እስካሁን ድረስ የሚገርመኝ በዛ ወቅት በወር ከሚከፈለን 80 ብር ደሞዝ አዲስ አበባ ለሚኖሩት እናቱ ተቆራጭ ያደርግ ነበር ሌላ ከሱ ውጭ ለቤተሰቡ ተቆራጭ የሚያደርግ ከኛ መካከል ማንንም አላቅም።
የጃኬቱን ወይም የሸሚዙን ኮሌታ ማቆም የሚወደው ነብሮ በዛን ግዜ ኮሌታ ማቆም ፋሽን ነበር መሰለኝ ሲራመድ ነጠር ነጠር የሚል ዘናጭ ንቁ ወታደር ነበር።
ጠምንጃ ሲያነግት ገንባሌ መለዮ አደራረጉ የራሱ መንገድ አለው የዝላይ ጫማው የሚያበራ ከስክሱ የሚያብረቀርቅ ነበር።
በክፍለ ጦራችን ውስጥ የተመደቡ የሩሲያ መኮንኖች ረዳት የነረው ወጣት ወታደር በጦር ግንባር ስለተሰዋ እሱን ተክቶ ከሩሲያ መኮንኖች ጋር መስራት የጀመረው ገዘሃኝ ነብሮ በለመዳትን ጥቂት የሩሲያ ቋንቋ ቃላት እቤት እኔጋ ማታ ማታ መለማመጃ አድጎ ያስቸግረኝ ነበር።
ሁለታችንም በእድሜ እኩያሞች ነን የ አስራ ስመንት አመት ወጣቶች አንድ ምሽት በጦር ሰፈራችን ውስጥ ሰው ሁሉ ተኝቶ በውድቅት ምሽት ላይ ምክንያቱ ምን እንደሆነ አሁን በማላስታውሰው ምክያት በኔና በገዘሃኝ ነብሮ መካከል ጭቅጭቅ ተነሳና አለመግባባታችን ተባብሶ ከድንኩናችን ወተን መደባደብ ጀመርን ከዛም ገላጋይ ሳይመጣ ድብድባችንን ተውነውና ሁለታሽንም በዛች ትንሽ ድንኩአን ውስጥ ገብተን ተኛን በማግስቱ እኔም ሆንኩ ነብሮ የተደባደብን ቀርቶ የተኩአረፍም ሳመስል በዛች ትንሽ ድንኩን ውስጥ እንደ ወንድማማቾች መኖር ቀጠልን አስመራን ለቅቄ ወደ ደብረ ዘይት እስክሄድ ድረስ ከነብሮ ጋር በዛች ድንኩአን ውስጥ ኖርን።
ወደ ደብረ ዘይት ስሄድ ለእናቱ ደብዳቤ እዳደርስለት ሰቶኝ ስለ ነበር ስድስት ኪሎ አካባቢ የሚገኘውን መኖርያ ቤታቸውን በስት መከራ ፈልጌ አግቼ ደብዳቤውን ለናቱ ስሰጣቸው ገዛሃኝን ያገኙ ይመስል እናቱ እንዴት ሰፍሰፍ ብለው እንደተቀበሉኝ አልረሳውም በቤታቸው ግድግዳ ላይ የኔ እና የነብሮ ፎቶ ተሰቅሎ አይቻለሁ ይህ የሆነው 1981 ዓም ታህሳስ ወር ነው።
ከዛ ቦሃላ እኔ እና ነብሮ የተገናኘነው ጦሩ ከተበተነ ቦሃላ ድሬደዋ መስመር ባቡር ላይ ነው ለዛውም ለጥቂት ደቂቃዎች ወድያው ተለያየን ሁኔታው ለሁለታችንም አመቺ አልነበረም ብዙም አላወራን።’ እንደዛው ነህ አልተለወጥክም’ አለኝ ነበሮ በተገናኘን ወቅት ካወራናቸው ነገሮች ውስጥ የማስታውሰው ደግሞም ሰፈራችን ለጎረቤታችን ለመደራችን በሬ አርጄ አከፋፈልኩ አለኝ ምናልባት አሁን ላይ ሳስበው ወደ ደቡብ አፍሪካ የመሰነባበቻ ይሆን ብየ አልኩ።
ከዚች በታች ያለችው መልክት ላባቢያን ሳይሆን ለነብሮ ነው።
ነብሮ አውቃለሁ ያኔም አስተውያለሁ አንድ የከበደ የከበረ አላማ እንዳለህ የተለየ ነገር ነበረህ አሁን በግልጥ ተረዳሁት በደመ ነፍስ ዝም ብለህ የማትኖር ስለ ቤተሰቦችህ ግድ የሚልህ ስለ አገርህ ልዩ ፍቅር ያለህ መሆኑን ገና ድሮ ያኔ አውቃለሁ።
እነዛን በኤርትራ ምድር ለሃገራቸው ክብር ዳር ድንበር የወደቁ ጉአደኞቻችን ሁሉ ትዝ አሉኝ ነብሮ የበማይሚዶ የተሰው ለጋ ወጣቶች ሞትህን ስሰማ ሁሉም ትዝ አሉኝ።
እነ መንገሻ ደሴ ፡ ስዩም ነጋሽ ፡ ደጃዝማች ዋቀዮ፡ እነ ተስፋሁን ፡ ዋለልኝ ለታ፡ ስንቱል ልዘርዝር ለአገራቸው በክብር ወደቁ አሁን ደግሞ አንተ ለምትወዳት አገርህ እንደጮክ እንደተሟገትክ በደቡብ አፍሪካ ወደክ። ነብሮ ያንተም ሞት የነዛ ጎአደኞቻችን ሞት አንድ ነው ለአገር ለወገን ለነፃነት ለዳር ድንበር !
SIR I SALUTE YOU!