ሱዳንና ኢትዮጵያ የጋራ ወታደራዊ ኃይል በማቋቋም የህዳሴውን ግድብ ለመጠበቅ ተስማሙ

አባይ ሚዲያ ዜና
አቢሰሎም ፍሰሃ

ሱዳንና ኢትዮጵያ የኢትዮጵያን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ለመከላከል የሚያስችላቸውን የጋራ ኃይሎች ለማቋቋም መስማማታቸው ታወቀ።

ስምምነቱን ተከትሎ ባሳለፍነው አርብ አዲስ አበባ ላይ የሁለቱ ሃገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ከማል አብዱል ማሩፍ አልማሂ እና ጀነራል ሳሞራ ዩኑስ በአገራቱ መካከል የተፈረመውን የመከላከያ ፕሮቶኮሎች እና የጋራ ጉዳዮችን አስመልክቶ ውይይት ማድረጋቸው ተሰማ።

በስምምነቱ የተገኘውን ውጤት ማክበር እና የድንበር አካባቢን ማጠናከር፣ የመረጃ ልውውጥ እና ቁጥጥር፣ የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የጦር መሳሪያዎች ንግድ፣ የአደገኛ መድሃኒቶች ዝውውር እና ጊዜያዊና ድንገተኛ ወንጀሎች መከላከል የውይይታቸው አጀንዳዎች እንደነበሩ ለማወቅ የተቻለ ሲሆን በተጨማሪም ሰላምን እና መረጋጋትን ለማስጠበቅ፣ በጋራ ትብብር እና ልምዶች መለዋወጥ፣ የጋራ ወታደራዊ ኃይሉን ለማንቀሳቀስ እና ለማገዝ ተስማምተዋል።

እንደሚታወቀው የህዳሴው ግድብ ከሱዳን ድንበር 20 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ነው እየተገነባ ያለው። የግድቡ ግንባታም ሱዳንን ጨምሮ ኢትዮጵያ እና ግብጽ መካከል ውጥረት አስፍኗል።

ካይሮ የህዳሴ ግድብ በግብፅ ዋናው የውሃ ምንጭ በሆነው በአባይ ተፋሰስ ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተፅእኖ ያስፈራኛል ስትል፤ አዲስ አበባ በበኩሏ ግድቡ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያስገኝ እና በተለይም የኤሌክትሪክ ኃይልን ማመንጨት በሚጀምርበት ጊዜ በተፋሰሱ ሀገሮች፣ ሱዳን እና ግብፅ ላይ ምንም አይነት ችግር አይፈጥርም ትላለች።