መንስር እና መንግስት (state & amp; government) በቅጡ ይለይ (በኣረጋዊ በርሀ)

በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ምህደራ (governance) ዙርያ መንግስታዊ-ስርዓትን (መንስር) እና መንግስትን በተመለከተ በርካታ ተመራማሪዎች ተከታታይ ጥናታዊ ጽሑፎች እያበረከቱ የሚያስነብቡን ቢሆንም፣ ከጉዳዩ ውስብስብነት የተነሳ ይመስላል፣ መንስር እና መንግስት በውል ተለይተው ስራ ላይ የዋሉበት ወቅት የለም ማለት ይቻላል። መንስር ሲባል በኣንድ ጂኦግራፍያዊ ክልል የሚኖር ማሕበረሰብ ለራሱ ደህንነትና እድገት ሲል የሚመሰርተው ዘለቄታና ተገቢነት (legitimacy) የተላበሰ ግዙፍ ተቋም ሲሆን፣ መንግስት ደግሞ እንደ ስራ-ኣስፈጻሚ ኣካል ሆኖ በመንስር ውስጥ የሚካተት ሓይል ነው። ያም ሆኖ መንግስት እንደ ብቃቱና ተቀባይነቱ በየጊዜው ሊለወጥ የሚችል ኣካል በመሆኑ፣ ከቋሚው መንስር ለየት ብሎ መታየቱ የግድ ነው። ይህ የመንስር እና መንግስት የተወሳሰበ ግኑኝነት በማያሻማ መልኩ ተብራርቶ ኣለመቀመጡ፣ እንደ ‘ማግና ድር’ የተቆራኘው የመንስርና የማሕበረሰቡ  ዝምድና እንዲሸረሸርና፣ መንግስት ሃላፊነቱን ያለኣግባብ እንዲጠቀምበት ማስቻሉን በብዙ መልኩ መገንዘብ ይቻላል፤ ለምሳሌም የኢህአዴግ ድርጅት በኣንድ ጊዜ፣ እንደ ፓርቲም እንደ መንግስትም እንደ መንስርም ሆኖ ስልጣን በማግበስበስ እየገዛ በስልጣን መባለጉንና ማሕበረሰቡንም ክፉኛ መጉዳቱን የምንገኝበት ሁኔታ ከማስረዳቱ ኣልፎ፣ ኢህኣዴግ ራሱም የግምገማ ሰሚናሮች በማካሄድ ግልጽ ስላደረገው ብዙ ኣያከራክርም። ኣሁን ኢትዮጵያ በስርዓት ለውጥ ዋዜማ ላይ ትገኛለች፤ የለውጡ ኣቅጣጫ ሳይዛነፍ ህዝቡ የሚበጀውን ስርዓት ይመሰረት ዘንድ የሁላችን የተባበረ ጥረት ይጠየቃል። ለውጡ ኣመርቂ ሆኖ ወደ ህዝባዊ-ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ልንሸጋገር ከተፈለገ የጋራውን መንስር ከነተቋማቱ መመስረት የመጀመርያው ስራ መሆን ኣለበት። በዚያው መሰረት ላይ በመቆም የተፈለገውን ዓይነት መንግስት መሰየም፣ ሲያስፈልግም መለወጥ ይቻላል። ይህን ሂደት በዚች ኣጭር ጽሑፍ ኣሟልቶ ማቅረብ ባይቻልም፣ ሓሳቡን ለውይይት ማቅረቡ ግን ወቅታዊም ኣስፈላጊም ነው ።

የመንስር ኣመጣጥና ከመንግስት ጋር ያለው ግኑኝነት፣

የመንስር ኣፈጣጠር የሚያሳየው፣ ከጥንቱ ሰዎች እንደ ማሕበረሰብ ሲሰባሰቡ ጀምሮ ቁሳዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶቻቸውን በቀጣይነት ይሟላ ዘንድ “በመግባባት” የፈጠሩት ተቋም መሆኑ ነው። ጥንታዊው መንስር ከብሄራዊነት ቀድሞ በወቅቱ በነበሩ ማሕበረሰቦች የተፈጠረ የምህደራ ስርዓት ሲሆን ከማሕበረሰብ እድገት ጋር ኣብሮ ኣድጓል። በመካከለኛውና በኣሁኑ ዘመንም፣ ማሕበረሰቦች በሚኖሩበት ጂኦግራፍያዊ ክልል (ሃፀያዊ-ግዛት ወይም ሃገር) ውስጥ ደህንነታቸውና እድገታቸው እንዲሁም ግኑኝነታቸው ያለ ግጭት ተጠብቆ እንዲቀጥል ሲባል የመንስርን የበላይነት ተቀብለው እንዲኖሩ የግድ ሆኗል። ከዚህ የተነሳም መንስር ኣስገዳጅነትና ተኣማኒነት የተላበሰ ብቸኛ ሓይል እየሆነ እንደመጣና እንደ ኣምር (concept) ደግሞ በኣብዛኛዎቹ ልሂቃን ተቀባይነት እንደተላበሰ ይታያል። በዚህ ሂደት መንስር ዘርፈ-ብዙ ተቋም ለመሆን ችሎ፣ በፈጠሩት ማሕበረሰቦች ላይ ቁጥጥሩን እያሰፋ ኣድጓል።  ኣንዱ ዘርፉ መንግስት ሲሆን ሲቪል-ማህበረሰብ፣ ዜግነት፣ ብሄራዊነት፣ ሕጋዊነት/ተኣማኒነት፣ ሉዓላዊነት፣ … የተሰኙ ሰፋፊ ኣምሮችም ከመንስር ጋር ቀጥታዊ የሆነ ተያያዥነት ኣበጅተው ኣድገዋል። ይህ ሂደት የመንስር ውስብስብነትና በዙርያው ኣያሌ የሓሳብ ትግሎች እንደተካሄዱበት ያመላክታል።

ኣሁን መንስር  ብለን የሰየምነው፣ ስቴት (state) የሚለው ቃል ራሱ ከላቲኑ ስታቱስ (status) የተመዘዘና ትርጉሙም ቁመና ወይም የኣንድ ሁኔታ ቋሚነት ማለት ሲሆን፣ በተያያዘ መልኩ የስርዓተ-መንግስትን (መንስር) ቋሚነት ለማመልከት ታስቦ የተቀመረ ነው። የኣምሩ ፍቺ በጣም ሰፊ ቢሆንም፣ ከዚህ ቀጥሎ መንስር (state) ስንል የኣንድ ጂኦግራፊያዊ ኣከባቢ ሰዎች በቋሚነት የሚገለገሉበት ስርዓተ-ምሕደራ ለማለት ነው። በሌላ ኣነጋገር መንስር ስንል ሕጋዊ ሓይል የሚጠቀም የኣስተዳደር ተቋም ለማለት የቀመርነው ቃል ነው። በውስጡም የሕግ ኣካላት፣ የሃገር-መከላከያ፣ የሰላም፣ የምርምር፣ የመሰረታዊ ልማት ግንባታ፣ የቢሮክራሲ መዋቅር…የመሳሰሉ መለስተኛ ተቋማት ይገኙበታል። ይህ መንስር የተሰኘው ዘርፈ-ብዙ ተቋም መንግስት ኖረ-ኣልኖረ፣  ዘመን-ተሻጋሪ የሆነ ሉዓላዊ ሓይል ነው። ስለዚህ ባጭሩ መንስር ሲባል በቀላሉ የማይለወጡና ለማሕበረሰቡ ደህንነትና እድገት የሚያስፈልጉ የጋራ መተዳደርያ ተቋማት ያቀፈ፣ ተቀባይነትም የተጎናጸፈ ሕጋዊ (ተገቢ) ሃይልም ነው።

የባላባታዊ ኣገዛዝ ባንሰራራበት በመካከለኛው ዘመን፣ መንስርና መንግስት ለያይቶ ለማየት ኣስቸጋሪ ነበር። ምክንያቶቹ እዚህ ኣጭር ፅሑፍ ማካተት ባይቻልም፣ የዛው ፖለቲካዊ-ባህል ቅሪት ይመስላል፤  በሃገራችን ኢትዮጵያም እስካሁን ድረስ መንስር፣ መንግስትና መሪው ጭምር በኣግባቡ ተለይተው ሃላፊነታቸውን የሚወጡበት ስርዓተ-ምህደራ መመስረት ኣልተቻለም። ከፍተኛ እድገት ባስመዘገቡ ሃገራት ግን በተለይ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ ባለው ጊዜ፣ ከባድ የስነ-ሓሳብ ትግል ተካሂዶበት ዘመናዊው መንስር (modern state) በመከሰቱና የበላይነት በመቀዳጀቱ ከመንግስት ጋር ያለውን ግኑኝነትና ልዩነት እየለየለትና ግልፅ እየሆነ መጥቷል። በዘመናዊ መንስር ምሕደራ ስር የህዝብ ድምፅ ወሳኝ ሚና ስላለው፣ ኣንድን መንግስት እንደ ብቃቱ ተኣማኒነቱ ሊለወጥ ወይም ሊቀጥል ይችላል፤ ነገር ግን መንግስት ይለወጥ እንጂ መንስር ቋሚ ሆኖ ይቀጥላል። ለመንግስታት መለዋወጥም ይሁን ቀጣይነት ደንብና ስርዓት ኣስያዢው መንስር ነው። በዘላቂ ይዘቱና የበላይነቱ መንስር ከተለዋዋጩ መንግስት ይለያል። ዝርዝር ይዘቱም ሕገ-መንግስት በተሰኘው ሰነድ ሰፍሮ፣ ይህ ሰነድ የበላይ ሕግ ሆኖ ያገለግላል።

 በዚህ ረገድ ዘመናዊው መንስር መሰረታዊና ዘላቂ ስራዎቹን ያለማቋረጥ እንዲያከናውን ሲችል፤ መንግስት ደግሞ በስራ-ኣስፈጻሚነት ተወስኖ፣ በስልጣን ዘመንም እየተገደበ እንዲያገለግል ተችሏል። ይህ ዓይነት የመንስር እና መንግስት ግኑኝነት በቅጡ መለየት የቻሉ ማሕበረሰቦች በተረጋጋ የእድገት ሂደት እንዲሰማሩና የኑሮ ህይወታቸውን ኣሻሽለው ለሌላም ሲተርፉ ፍንትው ብለን እንድናይ ተገደናል። እኛስ ምን ነካን ? የሚል ጥያቄ ኣንስተን ወደ ቀጣዩ ርእስ እንዝለቅ።

መንስር እና መንግስት በኢትዮጵያ፣

ወደ ዘመናዊው መንስር ባይሸጋገሩም፣ ቀደምት መንስር በመባል የሚታወቁት ስርዓተ-ምህደራዎች በተለያዩ የኢትዮጵያ ማሕበረሰቦች ውስጥ ተመስርተው እንደነበር በያካባቢው ያሉት ታሪካዊ ቅርሶች ያስረዳሉ። እነዛ ቀደምት መንስሮች የየራሳቸው ኣስደናቂ ታሪካዊ ስልጣኔ ያስመዘገቡ ቢሆንም ኣንዱ መንስር እየጎለበተና እየገነነ ሌላኛው እየተዳከመና እየከሰመ ሄደው በሂደት ኣንድ የኢትዮጵያ መንስር ኣይሎ ወጥቷል።  ቢሆንም ይህ የኢትዮጵያ ቀደምት መንስር ወደ ዘመናዊ መንስር መሸጋገር ኣቅቶት መንስር እና መንግስት ተደራርበው የሚጓዙበት ኣሮጌ ስርዓት ውስጥ ተጠምደን እንገኛለን። ይህ የመንስር እና የመንግስት የተመሰቃቀለ ጉዞ በማሕበረሰቡ ላይ ኣሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ ኣሁን ድረስ በመዝለቁ ለመንገኝበት ኋላ-ቀር ምሕደራና ጎስቋላ ኑሮ ተዳርገናል።

በሌላ ኣነጋገር፣  መንስር እና መንግስት ቋሚና ጊዜያዊ ባህሪያቸው ተለይቶ፣ እንደዚሁም ሓላፊነታቸው በመዋቅር ደረጃ ተገድቦ ተግባራቸውን ካላከናወኑ፣ እዛው- በዛው ዜጎችም መብታቸውና ግዴታችው ኣውቀው ብኣግባብ ካልተሳተፉ የተረጋጋ ኑሮ ይሁን ቀጣይ እድገት ኣይታሰብም። ከዛም ኣልፎ ሃገሪቱ የትርምስና የግጭቶች ቀጠና ሆና ማሕበረሰቡ ጭራሽ መንስር-ኣልባ እስከመሆን ሊደርስ እንደሚችል በርካታ ኣሳዛኝ ኣብነቶች መጥቀስ ኣይከብድም።

ዘመናዊት ኢትዮጵያን ስናስብ የመንስር እና የመንግስት ውስብስብ ግኑኝነት በንድፈ-ሓሳብ ይሁን በተግባር ለይቶ  ለማየት እስካሁን እንዳልተሳካልን ኣከራካሪ ኣይመስለኝም። እንዲውም ሌላውን እናቆየውና፣ በሃገራችን ቋንቋዎች ለ“ስቴት” (state) የሚመጥን ቃልም እስካሁን ኣልተገኘለትም። “ስቴት” በሃገራችን ስም ስላልወጣለት በ”መንግስት” ተሸፍኖ ወይም ተተክቶ እየኖረ፣ የላቀ ሚናውን ጎልቶ እንዳይታይ ሆኖዋል። ለዚህም ነው በቅድሚያ “ስቴት ለሚለው የእንግሊዝኛው ኣምር (concept)  “መንስርሚለው ቃል እንዲተካ የመረጥነው፤ ይህም መንስር የተሰኘው ቃል መንግስት እና ስርዓትን በማዳቀል የተቀመረ ሲሆን መንግስታዊ-ስርዓት ለሚለው ጣምራ ኣምር በመተካት ያገለግላል ከሚል እሳቤ ነው።

የኢትዮጵያ ስርዓተ-ምሕደራ (መንስር) ራሱን የቻለ ስም አለማግኘቱና መንግስት ከተባለው ኣምር ጋር እየተደበላለቀ በመኖሩ፣ ከዛም ኣልፎ ኣንዴ በመለኮታዊ፣ ሌላ ጊዜ በሰርቶ-ኣደራዊ፣ በወቅቱ ደግሞ በ’ብሄር-ብሄረሰብና ህዝቦች’ ሽፋን እየተድበሰበሰ በመገኘቱ ኣስቸጋሪ ኣዙሪት ውስጥ ገብተን ስንማቅቅ ዘመናት ኣስቆጥረናል። ወቅታዊውን “ሕገ-መንግስት” ስናይ፣ መንስር እና መንግስትን በቅጡ ሳይለይ ሉዓላዊው ስልጣን ለስሙ “የብሄር-ብሄረሰቦችና ህዝቦች” ነው ይላል። ይህ መመዘኛው ተለይቶ ያልታወቀ የሶስትዮሽ ስብስብ፤ ስልጣኑን ለፓርላማ፣ ፓርላማው ደግሞ ለፓርቲው፣ ፓርቲው ለሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ ም/ቤቱ ለጠ/ሚ (ኣንድ ሰው) ኣስረክቦ፣ ሃገሪቱ ያንድ ሰው ርስት ትመስል ስትታመስ ኖራለች። የዴሞክራሲ ተቋማትና ሲቪል ማሕበረሰቦች እንዳይንቀሳቀሱ በኣዋጅ የታገደበት ሃገር ፤ ለምርምር፣ ለፈጠራና እድገት ምንጭ የሆነውን የሓሳብ ነፃነት የተከለከለ ህዝብ እንዴት ተብሎ ከጎስቋላ ኑሮ ሊላቀቅ ይችላል! በዚህ ምህደራ የተነሳ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በኣሳፋሪ ኑሮ እንዲጠመድ መገደዱ ብቻ ሳይሆን ተከፋፍሎ እርስበርስ እተጋጨ ለባለስልጣኖቹ የተመቻቸ ተገዥ እንዲሆንም መደረጉን  ለመገንዘብ ኣይከብድም። ኣሁን ግን እጅግ ዘግይቶ ቢሆንም በዚሁ ምስቅልቅላዊ ምህደራ መቀጠል ወደማይቻልበት ወቅት ደርሰናል።    

ሰሞኑን ኣዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ኣብይ ኣሕመድ ካስደመጡን ተስፋ ጫሪ ንግግሮች ውስጥ ይህ “መንስር እና መንግስት (state & government) በቅጡ ይለይ !” የሚለው ጉዳይ በቀጥታ ባይነሳም ጥሪውን ለማስተናገድ በሩን እየከፈቱ ያሉ ይመስላል። ከዚህ እምነት በመነሳት ለዘመናዊ ምህደራ የመኣዝን ድንጋይ የሆነውን የመንስር እና መንግስት ተለያይቶ የማዋቀሩ ስራ ቅድሚያ እንዲያገኝ ያስፈልጋል እንላለን።

እንግዲህ እንደ ሃገር ስናስብ ሁላችንን (ገዢውም ተገዢውም / ፖለቲካ ማሕበረሰብም ሲቪል ማሕበረሰብም) የሚመለከት አንዱ ትልቁ ችግር፣ በጋራ የምንተዳደርበት ቋሚ ስርዓተ-መንግስት (መንስር) አለመኖሩ ነው ብለናል። ይህ ከገዢውም ከተገዢውም በላይ የሆነው ቋሚ መንስር በሁለት እግሩ ካልቆመና መንግስትን በኣግባቡ ገድቦ ካላሰራ፣ ለማደግ ይቅርና አብሮ በሰላም ለመኖርም አስቸጋሪ እንደሆነ ሩቅ ሳንሄድ ከቤታችን ወይም ከጎረቤቶታችን መረዳት ችለናል። ያለቅጥ ለተንዛዛው ችግራችን ኣንዱ ትልቁ ምክንያት በጋራ የምንተዳደርበት ስርዓተ-ምሕደራ ማለትም ዘመናዊ መንስር ኣለመመስረታችን መሆኑን ከላይ ኣመላክተናል።

በተጫኑብን ሕገ-መንግስቶች ውስጥ ለስሙ ቢነሳም፣ እስካሁን ድረስ የመንስርን የበላይነት ተቀብሎ ከስራ ኣስፈጻሚው ኣካሉ (መንግስት) ጋር ያለውን ልዩነት ኣስረግጦ በቅጡ እንዲደነገግና የተግባር መመርያ እንዲሆን ያደረገ ወገን ኣልነበረም። ይህ ክፍተት ካልተሞላ ደግሞ መንግስታዊ ስልጣን የሚቆጣጠሩ ወገኖች፣ ያለ ልጓም እንደሚከንፍ ፈረስ፣ ልቅ ሊሄዱ በሩ ክፍት ነው። ከዛም ኣልፎ ባለስልጣናቱ ከስግብግብ ከበርቴዎች ጋር እየተሻሹ፣ ለባእዳን በዝባዦች ኣጋልጠው ሊሰጡን እንደሚችሉ ተገንዝበናል። ኣሁንም መንስር እና መንግስት ልካቸው ታውቆ ገደብ ካልተበጀለትና ማሕበረሰቡም በየሲቪል ማሕበራቱ ኣማካኝነት ተደራጅቶ መሳተፍና መቆጣጠር ካልቻለ፣ ኣንድ ፓርቲ ወይም ኣንድ መሪ ብቻውን፣ ቅን ሆኖ ቢነሳም ቅሉ፣ ሰፊው ህዝብ የሚመኘው መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ይቸግረዋል። ኢኮኖሚስቱ ነጋድራስ ገ/ህይወት ባይከዳኝ በ1910ቹ እንዳስጠነቀቁን “ህዝብ የዕድገት ለውጥን ለማምጣት በጋራ ከተነሳ፣ ጉዞው በኣንዳንድ ክፉ ሰዎች ኣይቀለበስም። ህዝቡ ይህነኑ ለውጥ ለማምጣት በጋራ ካልሰራ ደግሞ በኣንዳንድ ግለሰብ በጎ ምኞት ለውጥ ኣይገኝም። ስለዚህም ኣንድ መንገድ ብቻ ነው ያለው። ኣንዱንና ብቸኛውን የዕድገት መንገድ ያልተከተለ ህዝብ ማለቁ ነው” ያሉት ኣሁንም ይሰራል (ሰረዝ ተጨማሪ)።  ይህ የተወሳሰበ ችግር የኢትዮጵያ ብቻም ኣይደለም፤ ዘመናዊ መንስር ባልመሰረቱ የኣፍሪቃ፣ ኤስያና ደቡብ ኣሜሪካ ሃገራት በስፋት ይታያል። መንስር የፈረሰባቸውን ቀርቶ የደከመባቸውንም ሃገሮች ስናጤን ምንኛ ማደግ እንደተሳናቸውና ህዝቦቻቸውም እንደሚጎሳቆሉ ከታሪክም ከወቅታዊ ክስተትም መገንዘብ ኣይከብድም። ኣንዱ ካንደኛው ቢብስበትም፣ ዘመናዊ መንስር መስርቶ የመንግስትን ልክ – በማይነቃነቅ ሃዲድ ውስጥ ገብቶ እንደሚሽከረከር ባቡር – እስካልተገደበ ድረስ ከችግሩ ኣዙሪት መገላገል ኣይቻልም። በኣንፃሩ ጠንካራ መንስር የመሰረቱ ሃገሮች፣ እንከን ኣይወጣላቸውም ባይባልም፣ ህዝቦቻቸውን ከኋላ-ቀርነትና ከጎስቋላ ኑሮ ኣላቀው ህዋ ላይ መጥቀው ድንቅ ምርምር ሲያካሂዱ እንታዘባለን።

ከዚሁ ችግር በተያያዘ መልኩ ለመጀመርያ ጊዜ መንስርን (ስቴት) ጠቅሰው ሲተቹ ያየኋቸው የታሪክ ልሂቅ ኣቶ ተክለጻድቅ መኩርያ ናቸው፣ ከእረፍታቸው በኋላ በቅርቡ በታተመው “የህይወቴ ታሪክ” በተሰኘው መጽሃፋቸው የሶስቱ መንግስታዊ ኣካላት ሓላፊነት ከዘመናዊ መንስር ጋር ያላቸውን ትሥሥር ሲገልፁ (ገጽ 258) “… ፫ቱ ኣቅዋሞች (ተቋሞች) ለየክፍላቸው ተለያይቶ የተሰጣቸውን መብት የተጣለባቸውን ግዴታ በትክክል በመምራት በመጨረሻ የሶስቱም ተግባር በኣገሪቱ የበላይ ኣቅዋም፣ ፈረንጆች ስቴት ብለው በሰየሙት እኛ ገና የኣማርኛ ቋንቋ ባላገኘንለት፣ ላይ ደርሶ ከተዋሃደ በኋላ በፍጻሜው የሚሰጠው ውጤት የሰውን ልጅ ከክፉ ኑሮ ላይ ኣላቆ በተሻለ የነጻነት ኑሮ ላይ ሊያስቀምጠው ቻለ። በዚህ ዓይነት በኣዲሱ ሕገ መንግስት ዜጋ ሁሉ ለኣገሪቱ በነፍስ ወከፍ ሃላፊዋ ነው። በተገላቢጦሽ የዚህ ስቴት የተባለው መሪ ከኣስተዳደር ሓላፊነት ነጻ ሆኖ ይኸው ኣዲስ ሁኔታ ከመወቀስና ከመታማት ነጻ ኣደረገው። በርሱ ፈንታ ህዝብ የመረጠውን ኣማካሪ ኣማካሪም የመረጠውን ኣስተዳዳሪ በመውቀስ ተወሰነ።” (ሰረዝ ተጨማሪ) ይሉና፤

ይህን ግንዛቤ ከሃገራችን ሁኔታ ጋር ሲያያይዙት ደግሞ (በገጽ 158) “ ‘እኛ ኢትዮጵያውያን መቼ ይሆን እንደዚህ ያለው እድል ላይ የምንደርሰው’ የሚል ኣሳብ ይመላለስብኛል። ከምክር ቤት ውጭ በኣገሪቱ በተደነገገው ሕገ መንግስት የተነሳ የህዝብ ወኪሎች በምክር ቤት ከምክር ቤት ውጭም፣ ጋዜጠኛውም ማናቸውም የሕብረተሰቡ ኣባል ያሰበውን ተናግሮ ጽፎ በመንግስቱ ላይ ነቀፋውን በመሰለው መንገድ ወርውሮ በነጻ ወደ ቤቱ መሄዱን፤ በምክር ቤት ምርጫ ኣንዱ ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴርነት ደረጃ የሚወጣው ባምቻ በጋብቻ ወይም በትእዛዝ ሳይሆን፣ ያስተዳደር ኣሳቡን ኣቅርቦ በፉክክር በልጦ ወደ ስልጣን ሲወጣ ሌላው ተነቅፎ ሲወርድ እያየሁ የዚህ ዓይነቱ ኣስተዳደር ካገራችን መራቁን፣ ንጉሰ ነገስቱ ብቻ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው የልባቸውን መስራታቸውን፣ ያገሪቱን ሃብታምነትና በደህና ኣስተዳዳሪ እጦት የተነሳም የህዝቡን ድህነት እያመዛዘንሁ ባገሬ መንግስት ኣስተዳደር ላይ  ያለኝ ጥላቻ እየባሰብኝ ሄደ።” በማለት ስም ያልወጣለት ስቴት፣ ኣሁን በቋንቋችን መንስር ያልነው ቁምነገሩንና ኣስፈላጊነቱን በሚገድ መንፈስ ያብራሩልናል።

የሁለቱንም አንጋፋ ልሂቃን መልእክት ስናቀናጀው፣ ሰላምና ዕድገት ከተፈለገ ለሁላችን የሚበጅ ስርዓተ-መንግስት (መንስር) በጋራ መመስረት የግድ እንደሚያስፈልግና፣ መንግስትም በመንስሩ ተገድቦ መስራት እንዳለብት ኣበክረው ያሳስባሉ። ይህ ካልሆነ ደግሞ ከችጋር መላቀቅ ቀርቶ ጭራሽ መበታተን ሊከተል እንደሚችል ግልጽ ያደርጋሉ። ዘመናዊው መንስር በጋራ ተሳትፎ ሲቋቋም ግን ስራ ኣስፈጻሚው መንግስት ከነ መሪው፣ ሕገ-መንግስት ላይ በሰፈረውና የመንስሩ ተቋማት ሊቆጣጠሩት በሚያስችል ደንብ መሰረት ያስተዳድራል፣ ይጠየቃል፣ ሲያስፈልግም ይለወጣል። በዚህ ሂደት ገንቢ ስራ በቀጣይነት እየተሰራ የሰውን ህይወት መቀየር ይቻላል፤ ሃገርም በእድገት ጎዳና ትጓዛለች። 

የዶ/ ኣብይ ተግዳሮች እና ኢህኣዴግ !

የህወሓት/ኢህኣዴግ ገዢ መደብ ለ27ዓመታት መንግስታዊ ስልጣን ይዞ በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያወረደውን መከራ እዚህ መዘርዘሩ ‘ለቀባሪ ማርዳት’ ይሆናል። የዚህ ገዢ መደብ ክፉ ኣገዛዝ ኣሁን ዶ/ር ኣብይ ካስደመጡን ህዝባዊ ኣመለካከቶች ጋር ጭራሽ የሚጋጭ ሆኖ ኣግኝተነዋል። ወደ ዝርዝር ሳንገባ፤ ስለ ሃገር ኣንድነት፣ ስለ ዴሞክራሲዊ መብቶች፣ ስለ ዜጎች ተሳትፎ የመሳሰሉትን መርሆች እንኳን ብናጤን ዶክተሩና ድርጅቱ ሆድና ጀርባ መሆናቸውን በግልጽ እንገነዘባለን። የዶክተሩ እሳቤ ገንቢ ሲሆን የድርጅቱ ተግባር ኣፍራሽ ነው። ገንቢ እና ኣፍራሽ ኣመለካክቶች ደግሞ ተጣጥመው ሊጓዙ  ባህሪያዊ ኣይደለም። ገንቢው እሳቤ የበላይነት ኣግኝቶ ተግባር ላይ ሊውል ከሆነ የቆየው ሓይል ከነኣመለካከቱ ለኣዲሱ ሓይል ቦታ መልቀቅ ኣለበት። ይህ የለውጥ ሂደት (ሽግግር) በቀላሉ የሚከናወን ባይመስልም በመጎልበት ላይ ያለው የለውጡ ማዕበል ለኣዲሱ ኣመለካከት ኣመቺ ንጣፍ መሆኑ በግልጽ ይታያል። ፉክክሩ በዚህ መልክ ቀጥሎ ኣዲሱ ኣመለካከት ኣይሎ መውጣቱ ባይቀርለትም፣ በመሰሪዎች ሳንካ ሳይደናቀፍ፣ ተኣማኒ ይዘትና ቅርጽ ተላብሶ እንደ ተቋም የሚታነጸው እንዴት ነው? ብሎ መጠየቅ የሁሉም በጎ ኣሳቢ ዜጋ ሃላፊነት ነው።

ለዚህ ከባድ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ወደ መንስር እና ሕብረተሰብ ዝምድና ብሎም ወደ ዘመናዊ መንስር ህንጸት እንድንገባ የግድ ይላል። ከላይ እንደተጠቀሰው ሕብረተሰቡ ቁሳዊና ስነ-ልቦናዊ ፍላጎቶቹ ተሟልቶለት፣ ያለ ስጋት በሰላም ለመኖር  ሲፈልግ ውጥኑን የሚያሳካለት ሓይል ያስፈልገዋል። ይህ ሓይል መንስር ብለን የሰየምነው ነው። የኣንድ ሃገር ሰዎች ኣስፈላጊነቱን ኣምነውበት ለመሰረቱት መንስር ሕጋዊ ሓይል ኣጎናፅፈው ይተዳደሩበታል። በዚህ መልክ ዘመናዊ መንስር የመሰረቱ ሃገሮች የተረጋጋና የበለጸገ ህይወት ሊመሩ ችለዋል። መንግስትን ወይም መሪውን መቀየር ሲያስፈልጋቸው እንኳን ጥሩ ልብስ እንደ መቀየር እንጂ ጦር የሚያማዝዝ ፈተና ኣድርገው ኣይመለከቱትም። የላቀ ምሳሌ ብንወስድ፣ በቅርቡ ጊዜ (ከ 1946-2018 ዓ.ም.ፈ.) ጣልያን በ 72ዓመታት ውስጥ 65 መንግስታት በሰላም ስትቀይር፣ ቤልጄም ደግሞ ከ2010-2011 ዓ.ም.ፈ. በነበሩት 541 ቀናት ያለ መንግስት እንደወትሮዋ በእርጋታ መቀጠል ችላለች። ይህ ሊሆን የቻለው የህዝቡን ኣመኔታ የተላበሰ፣ የተደላደለ መንስር ከቦታው ስላላቸው ነው። ኢትዮጵያም ተመሳሳይ ወይም ያንኑ ዓይነት መንስር እንዳይኖራት የሚያደርግ ምንም ምክንያት የለም። የተረጋጋና የበለጸገ ህይወት ለመመራት በጋራ ፍፅፅም የሚመሰረት መንስር የግድ ኣስፈላጊ ነው።

ይህ ከባድና ውስብስብ ሓላፊነት ባንድ ድርጅት ወይም ባንድ ግለሰብ የሚከናወን ኣይደለም፤ የብቁ ድርጅት ወይም የቅን ግለሰብ ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ዘላቂ የጋራ ሃገራዊ ጉዳይ ስለሆነ የሁሉንም የጋራ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው። ህወሓት/ኢህኣዴግ የጋራው ተሳትፎ እንዳይኖርና ዘመናዊው መንስር እንዳይቋቋም ጋሬጣ ሆኖ ቆይቷል፤ ህዝቡም በዛው መጠን ሲከፋና ሲቃወም ሃገራችን ኣጣብቂኝ ውስጥ ገብታ ወደ ፊት መራመድ ኣልቻለችም። ኣዲሱ ጠ/ሚኒስትር የድርጅቱን ኋላ-ቀር ኣካሄድ ተረድተው፣ የህዝቡን ዋይታ ኣድምጠው መፍትሄ ይገኝ ዘንድ ገንቢ ጥሪ በማስተጋባት በሩን እየከፈቱ ነው። ይህ በጎ ኣስተሳሰብ ተግባር ላይ ሊውል የሚችለው ገና ከጅምሩ መንስርን ከመንግስት በቅጡ ለይቶ ማቋቋም ሲቻል ነው። በርግጥ ይህ ከባድ ስራ ለኣንድ ሰው ወይም ለኣንድ ፓርቲ ብቻ የሚተው ኣይደለም፤ የሁሉንም ዜጋ ህይወት የሚነካ የቋሚ ስርዓት ግንባታ ጉዳይ ስለሆነ የጋራ ተሳትፎን የግድ ይላል። ስለሆነም ለጋራ እድገታችን ስንል መንስርን ከመንግስት ለይቶ በማቋቋሙ ሂደት በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም ልንተባበራቸው ያስፈልጋል። ከጅምሩ የተቃና ጉዞ መዳረሻውም ይቃናል።

ለማጠቃለል ያህል – ኣንድ ማሕበረሰብ ደህንነቱን መጠበቅ፣ እድገትን ማስመዝግብ ከፈለገ መንስር የተባለው ግዙፍ ተቋም መመስረትና በዚሁ ሓይል መተዳደር ግዴታ ነው።  በማሕበረሰቡና በመንስሩ መካከል ተገኝቶ ስራ-የሚያስፈፅም ኣካል መንግስት ሲሆን ደግ-ደጉ ሲሰራ የሚሞግስ፣ ሲያበላሽ ደግሞ የሚለወጥ ይሆናል። ይህ ስርዓተ-ምህደራ ባለመገንባቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ከኋላ-ቀርነትና ከችጋር ሊላቀቅ ኣልቻለም። ስለዚህ ይህን ዘመናዊ መንስር ያለ ዋል-እደር ለመመስረት ዜጎች መረባረብ ይኖርብናል። ይህ ገንቢ ውጥን እንዲሳካ መንግስታዊ ስልጣን የተረከበው የዶ/ር ኣብይ ፓርቲ ተፎካካሪ ያልዋቸውን ኣማራጭ ፓርቲዎች በመንስሩ ግንባታ እኩል እየተሳተፉ ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ ማስቻል ይጠበቅባቸዋል። መከናወን ያለባቸውን ቅድመ-ዝግጅቶችም በሶስት ነጥቦች ለማጠቃለል ይቻላል፣

1ኛ/ የፖለቲካና ሲቪል ማሕበረሰቡ እንደየ እምነቱና ፍላጎቱ ይደራጅ ዘንድ ምሕዳሩን ነፃ ማድረግ፤

2ኛ/ ለሁሉም የሚያስተናግድ መንስር  በጋራ ተሳትፎ ለማቋቋም መድረክ ማዘጋጀት፤

3ኛ/ መንስሩ በተቋቋመበት መርሆዎች መሰረት መንግስትን ሊያዋቅር የሚችል ብቁ ኣካል (ፓርቲ) እንዲመረጥ ማድረግ።

ከጅምሩ እንዲህ ከተነሳን በመንስር ታጅበን የሚመቸንን መንግስት ባስፈለገ ጊዜ እየሰየምን የተረጋጋ ህይወት ለመምራትና ኣብረን ለመበልፀ ኣይሳነንም።        

የኢትዮጵያ ትንሳኤ በጋራ ትግል እውን ይሆናል!!!

 (በኣረጋዊ በርሀ )- abmersha66@yahoo.com

May Day 2018

                                                                                                                             4