ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች አማራን ማፈናቀሉ እንደቀጠለ ነው

አባይ ሚዲያ ዜና
አቢሰሎም ፍሰሃ

ዛሬ ግንቦት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ዳኖ ወረዳ ውስጥ በአዋዲ ጉልፋና አጅላ ዳሌ ቀበሌዎች ለዘመናት ሲኖሩ የነበሩ ከ1,200 በላይ አባወራዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ተሰማ።

ከግንቦት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ በወረዳው እና በቀበሌው አመራሮች የተገደዱት ተፈናቃዮች «መሬቱን ለኦሮሞ ወጣቶች ማከፋፈል ስለምንፈልግ ለቃችሁ ወደ ምትሄዱበት ሂዱ» መባላቸውን ገልፀዋል።

ተፈናቃዮቹ ቀኑን በኢቲቪ እና ፋና በር ላይ ሆነው ከሐገር ከቀያችን በግፍ ተባረን ድምፃችንን የሚሰማን አካል አላገኘንም ቢሉም አሁንም ያነጋገራቸውም ሆነ የሚሰማቸው ሳያገኙ ውለው ማምሻውን ከተቋማቱ በር ላይ ወዴት እንደሄዱ አልታወቀም።

በአማራነታቸው ብቻ ለዘመናት ከኖሩበት በግፍና በሥቃይ ሀብት ንብረታቸውን ተቀምተው ከተፈናቀሉት ወገኖች አብዛኞቹ አውቶቡስ ተራ ከነቤተሰቦቻቸው መስፈራቸውም ታወቋል።

ይህ ዜና እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ የኦሮሚያ ክልልም ይሁን የፌዴራል መንግስት ዝምታን መርጠዋል።

በተመሳሳይ ዜና ከቤንሻንጉል መተከል ተፈናቅለው ባህር ዳር ሰፍረው ለሚገኙት አማራዎች በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ወገኖች ከ132 ሺ ብር በላይ ወጪ በማድረግ የብርድ ልብስ እና አንዳንድ ቁሳቁሶችን በመግዛት ለወገን ደራሽነታቸውን አስመስክረዋል።