በጠቅላይ ሚንስትሩ ጥይቄ ከእስር  የተለቀቁት ኢትዮጵያኖች ወደ አገር መግባታቸው ተገለጸ

አባይ  ሚዲያ ዜና

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሳውዲ ባደረጉት ይፋዊ የስራ ጉብኝት በሳውዲ በእስር የሚገኙ ኢትዮጵያኖች  ነጻ በሚለቀቁበት ጉዳይ ላይ መወያየታቸው ተገለጸ።

ከሳውዲው አልጋ ወራሽ ጋር በእስረኞቹ ጉዳይ ላይ ውይይት ከተደረገ በሃላ ወደ 1000 የሚደርሱ ኢትዮጵያኖች ከእስር እንደሚለቀቁ ተገልጿል።

ኑሮን ለማሸነፍ እና ቤተሰባቸውን ከችግር አረንቋ ለማላቀቅ ወጣት  ኢትዮጵያውያን ወደ ሳውዲ በመሰደድ በተለያዩ የስራ መስክ ተቀጥረው በሚሰሩበት ወቅት ለከፍተኛ ግፍ እና መከራ እየተጋለጡ እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

በተያያዘ ዜና ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሱዳን ባደረጉት የስራ ጉብኝት በሱዳን የታሰሩ ኢትዮጵያውያንን በነጻ እንዲለቀቁ ለሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኡማር አልበሽር ባደረጉት ጥያቄ መሰረት 1400 የሚደርሱ እስረኞች መለቀቃቸው ሲታወስ ከተለቀቁት ውስጥ   ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ፍቃደኛ የሆኑ  41 ኢትዮጵያኖች ወደ አገር መግባታቸው ተዘግቧል።

በኬኒያም በተመሳሳይ በእስር ቤት ውስጥ የነበሩትን ኢትዮጵያውያን እንዲለቀቁ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለኬኒያው ፕሬዝዳንት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ወደ 1600 የሚጠጉ ኢትዮጵያኖች ሲፈቱ ወደ ኢትዮጵያ በፍቃደኝነት የተመለሱ ቁጥር እስካሁን በግለጽ አልተገለጸም።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት እያሳየች እንደሆነ የተለያዩ ሪፖርቶች ቢያሳያሙ  በታሪኳ ህዝቦቿ በኢኮኖሚ እንዲሁም በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት ለስደት እና በስደት ላይ ለእንግልት፤ ለእስራት እንዲሁም ለመስማት ለሚዘገንን ግፍ የተዳረጉበት ወቅት ያለፈው   27 አመታት እንደሆነ ይነገራል።