የሳውዲ ባለስልጣናት 500 , 000 (አምስት መቶ ሺ) የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንን ለማባረር ዝግጅት ጀመሩ

አባይ ሚዲያ ዜና

የዶክተር አብይ አህመድ ጉብኝትን ተከትሎ የሳውዲ ባለስልጣናት በህገወጥ መንገድ ሳውዲ ውስጥ ይገኛሉ በማለት የፈረጁዋቸውን  ግማሽ ሚሊዮን (አምስት መቶ ሺ) ኢትዮጵያውያንን ለማባረረ ዝግጅት መጀመራቸው ተገለጸ።

በእስር የነበሩ ወደ 1000 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንን እንዲፈቱ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ያቀርቡትን ጥያቄ ያለማንገራገር በደስታ የተቀበለው የሪያድ መንግስት ኢትዮጵያውያኑን በመፍታት በአፋጣኝ ሳውዲን ለቀው ወደ ኢትዮጵያ በበረራ እንዲመለሱ አድርጓል።

ከእስር ከተለቀቁት ኢትዮጵያውያን መካከል ወደ 690 የሚደርሱ አዲስ አበባ መግባታቸውን በማሳወቅ ወደ የቤተሰቦቻቸው እንደሚላኩ መንግስት አሳውቋል።

የሪያድ ባለስልጣናት የጠቅላይ ሚንስትር የዶክተር አብይን ጉብኝት እና እስረኞች እንዲፈቱ የቀረበውን ጥያቄ በመታከክ በሳውዲ በህገወጥ መልኩ ህይወታቸውን እየገፉ ይገኛሉ የተባሉ ወደ 500, 000 (አምስት መቶ ሺ) የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንን በግዳጅ ወደ አገር ለመላክ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ተዘግቧል።

በሙስና ክስ በሳውዲ በቁጥጥር ስር ያሉት ቢሊየነሩ ሼህ ሙሀመድ አሊ አልአሙዲን ለማስፈታት የተደረገው ስምምነት ውጤታማ እንደሚሆንም ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ከሳውዲው አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ጋር በሼህ አላሙዲን ጉዳይ  መወያየታቸውን ገልጸው የሙስና ክስ ቀርቦባቸው በቁጥጥር ስር ያሉት ሼህ መህመድ በቅርብ ጊዜ ይለቀቃሉ በማለት መግለጻቸው ይታወሳል።

ከሼህ ሙሀመድ አሊ አልአሙዲን በተጨማሪ በሃብት ብዛት በሳውዲ በቀዳሚ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቢሊየነሩ ልኡል አልዋለድ ቢን ታላል በሙስና ክስ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ሲሆን ከሳውዲ መንግስት ጋር ባደረጉት የገንዘብ ድርድር ከወራት በፊት ከእስር መለቀቃቸው ሲታወስ ከእስር ነጻ ለመውጣት ከመንግስት ጋር የተደራደሩት የገንዘብ መጠን ግን በይፋ አልተገለጸም።

በሃብት በናጠጡ ባለሃብቶች እና ልኡሎች ላይ የጸረ ሙስና እርምጃ የከፈቱት አልጋ ወራሹ መሀመድ ቢን ሳልማን እስካሁን ከ100 ቢሊየን ዶላር በላይ ከባለሃብቶቹ መሰብሰባቸው የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ሼህ ሙሀመድ አሊ አልአሙዲ በኢትዮጵያ በተለያዩ የንግድና የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተው ሲገኙ ህውሃት ስልጣን ላይ እንዲመጣ ከፍተኛ እርዳታ እንዳደረጉና የአገዛዙም ቀኝ እጅ ሆነው መቆየታቸው ይነገራል።