የወልቃይት የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሜቴ ከቤንሻንጉል ለተፈናቀሉት ወገኖች የገንዘብ እርዳታ ሰጠ

አባይ ሚዲያ ዜና

ከቤንሻንጉል የተፈናቀሉትን የአማራ ተወላጆች ለመርዳት የሚደረገው ርብርቦሽ እየቀጠለ ሲገኝ የወልቃይት የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ከቤንሻንጉል ለተፈናቀሉት ኢትዮጵያኖች የገንዘብ እርዳታ ለግሷል።

በአቶ አታላይ  ዛፌ የተመራው የወልቃይት የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ከወልቃይት ተወላጆች የተሰበሰበ እና ለተፈናቀሉት ወገኖቻችን እርዳታ የሚውል ሰላሳ ሺህ ብር አበርክቷል።

አምላክ አገራችንን ኢትዮጵያን የሰጠን በጋራ እንድንኖርባት እንደሆነ በመግለጽ በተፈናቃዮቹ እየደረሰ ያለውን መከራ የመንግስት አካላት አይተው ተገቢ ምላሽ እስኪስጡ በትግስት እንደሚጠብቁ የወልቃይት የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሜቴ የሆኑት አቶ አታላይ ዛፌ በእርዳታ አሰጣጡ ፕሮግራም ላይ ተናግረዋል።

የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች የሚገኙበት አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው  እና የተፈናቃዮቹ ጉዳይ እንቅልፍም እንደነሳቸው የገለጹት አቶ አታላይ ዛፌ በየትኛውም የአለም ክፍል ያለ ኢትዮጵያዊም በተፈናቃዮቹ የደረሰውን ግፍ ሲሰማ ያመዋል በማለት ገልጸዋል።

ከአቶ አታላይ ዛፌ በተጨማሪ በአገዛዙ በእስር የነበረችው አክቲቪስት ንግስት ይርጋ፣ አቶ አለነ ሻማ እንዲሁም አቶ ጌታቸው አደመ  ከቤት ንብረታቸው ከቤንሻንጉል በግዳጅ እንዲፈናቀሉ የተደረጉትን የአማራ ተወላጆችን ጠይቀዋል።

የተፈናቀሉትን የአማራ ተወላጆች ለመርዳት በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከ 130 ሺህ ብር በላይ በማሰባሰብ የቁሳቁስ ግሺ ማድረጋቸው ሲታወስ በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማህበር አቅፎ የሚንቀሳቀሰው ግሎባል አሊያንስ ወደ 800 ሺህ ብር እርዳታ መለገሱ አይዘነጋም።