የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር አመራሮች አዲስ አበባ መግባታቸው ታወቀ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
አቢሰሎም ፍሰሃ

ዛሬ ግንቦት 15 ቀን 2010 አ/ም አዲስ አበባ የገቡት የቀድሞው ኦነግ የአሁኑ ኦዴግ አመራሮች አምስት እንደሆኑ ታወቀ።

የኦዴግ ሊቀ መንበር የሆኑትን አቶ ሌንጮ ለታ እና ምክትል ሊቀ መንበሩ ዶ/ር ዲማ ነገዎን ያካተተው ይሄው ልዑክ አቶ ሌንጮ ባቲ፣ ዶ/ር ሐሰን ሑሴን እንዲሁም ዶ/ር በያን አሶባን ይዞ ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ አየር መንገድ ሲደርስ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት ጉዳዮች አማካሪ አቶ አባ ዱላ ገመዳ፣ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የግንባሩ ሊቀ መንበር ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችም መልስ ሲሰጡ እኛ መንግስትን ለማግኘት እና ለመወያየት ሙከራ ከጀመርን ስድስት አመት ሆኖናል ብለዋል። በዝቅተኛ ደረጃ ለአመታት ብዙ ግንኙነት እንደነበራቸውና ከመንግስት ጋር በነበራቸው ያለመስማማት አዲስ አበባ ድረስ መጥቼ ሳይሳካ ተመልሻለው ያሉት ሊቀመንበሩ በዝቅጥኛ ደረጃ ያሏቸው እነማን እንደሆኑ ሳይናገሩ አልፈዋል።

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የለውጥ ሂደት የፈጠረውን እድል ተጠቅመን ከመንግስት ጋር ተወያይተን ወደ እዚህ ለመደራደር መተናል ያሉት ሊቀመንበሩ ጋዜጠኛው ከመንግስት ጋር የተነጋገራችሁባቸው ነጥቦች ምንድን ናቸው? አሁንስ የምትነጋገሩባቸው እንዲሁም የእናንተ የወደፊት ተሳትፎ ምን ይሆናል ብሎ ላቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ሌንጮ ከዚህ አገር ከወጣን አመታት ሆኖናል፤ አገሪቷ ደግሞ በኢኮኖሚ፣በማህበረሰብ እና በፖለቲካ በአፋጣኝ ሁኔታ እየተቀየረች ስለሆነ ሁኔታዎችን በጥልቀት ከመረመርን በሗላ የወደፊቱን ተሳትፎአችንን ወስነን ወደ ስራ እቅድ ማውጣት እንሸጋገራለን ብለዋል።

ሲቀጥሉ እዚህ ከመምጣታችን በፊት ከመንግስት ጋር ያደረግናቸው ውይይቶች ስለ አመጣጣችን ብቻ ነው። ሰፋፊ የሆኑ አነታራኪ የፖለቲካ ጉዳዮች አልተነሱም እነሱን እዚህ አንስተን እንወያይባቸዋለን ብለን ነው የወሰነው ሲሉ ተናግረዋል።

ምክትል ሊቀመንበሩ በበኩላቸው የመጡበትን አላማ ሲናገሩ እንደ አንድ ሰላማዊ ፓርቲ ተመዝግበው ለመንቀሳቀስ እንደሚፈልጉና ካልሆነ ደግሞ ከሌላ መሰል ፓርቲ ጋር ተዋህደው ለመስራት እቅድ እንዳላቸው በመግለጽ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችም ከትጥቅ ትግሉ ወጥተው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ትግላቸውን ቢያካሂዱ የተሻለ ስለሆነ እነሱን ለማግባባት እየሰራን ነው ይሳካልናል ብለንም እናምናለን ሲሊ ተደምጠዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴም “ህገመንግስታዊ ስርዓቱን” የተቀበሉ ሃይሎች መግባት አለባቸው በማለት ህገመንግስታዊ ስርዓቱ ሁሉንም በሚያሳትፍ መልኩ እንዲከለስ የሚቀርበው ጥያቄ ተቀባይነት እንደሌለውና ገዢው መንግስት ለድርድር ያስቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ አለመለወጡን አመላክቷል።