አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ነጻ እንደሚወጡ ተገለጸ

አባይ ሚዲያ ዜና

የነጻነት ታጋይ ተብለው በብዙሃኑ የተሰየሙት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር መለቀቃቸው የማይቀር እውነታ እንደሆነ ተሰማ።

የግንቦት ሰባት ድርጅት መስራች እንዲሁም ድርጅቱን በዋና ጸሃፊነት ያገለገሉት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከተደላደለ የለንደን ኑሮዋቸው በረሃን በመምረጥ አገዛዙን ለመፋለም የቆረጡ እንደሆኑ ይታወሳል።

አገዛዙ የነጻነት ታጋዩን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በማሰሩ ኢትዮጵያን ከመጥቀም ይልቅ ለከፍተኛ ኪሳራ እንደዳረጋት ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገልጸዋል።

የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መታሰርን ተከትሎ ኢትዮጵያ ልታገኘው የሚገባውን በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ልታጣ እንደተገደደች ዶክተር አብይ አህመድ በመጥቀስ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በቅርብ ቀናት ውስጥ ከእስር መፍታት ግድ እንደሆነ አሳውቀዋል።

የግንቦት ሰባት ከፍተኛ አመራር የነበሩትን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በቅርብ ቀናት ውስጥ ከእስር ለመልቀቅ እንደታቀደ  በቤተመንግስቱ ለውይይት ለተጋበዙት የትግራይ ተወላጆች ጠቅላይ ሚንስትሩ ባሳወቁበት ፕሮግራም ላይ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ማሰሩ ትክክል እንዳልነበረም እቅጩን ለነዚሁ ተሰብሳቢዎቹ ተናግረዋል።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በህውሃት የበላይነት ሲመራ የቆየው አገዛዝ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጽመውን ጭቆና እና የመብት ጥሰት በመታገል ነጻናት እና ፍትህ እንዲሰፍን ከፍተኛ መስዋትነትን ለመክፈል ቆርጠው የተነሱ መሆናቸው ይታወቃል።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከየመን ሰንአ አየር ማረፊያ  የአለም አቀፍ ህግን በሚጥስ መልኩ ታፍነው በመታሰራቸው  ምክንያት አገዛዙ ለከፍተኛ ገንዘብ እጦት ከመዳረጉ በተጨማሪ በሽምቅ ትግልም በርካታ ወታደሮችን  እንዲያጣ እንደተገደደ ይታወሳል።