እትት በረደኝ አልቻልኩም ባካችሁ፣
አንዲት ወንበር ብቻ ስጡኝ እባካችሁ።
ስደቱም መረረኝ ምንም አልተገኘ ፣
ሃሳቤም ከሸፈ ህልም ሆኖ ተገኘ ።
ልቻለው ትችቱን ወቀሳውን ሁላ ፣
ስትሉኝ ሰማሁኝ ይህ የሰው ዳውላ ።
ያላችሁትን በሉ እኔ ገብቻለው ፣
ለወያኔ ጓዳ እጅም እነሳለው ።
“ ሌንጨጮ”
ብለህ ገባህ በቃ ማሽቃበጡ አማረህ ፣
እንግዲህ ቃሊቲን ትሞክረዋለህ።
ብርዱ ጀማመረህ አሰኘህ ወይ ኩታ ፣
ጋቢ መቋጨቱም ሰለቸህ ወይ ማታ ፣
መቋደስ ያማረህ ከሸገር ጨዋታ ።
እንደው ምንስ ነካህ ምንስ ልታገኝ ፣
አንዱንም ሳታገኝ ሁሉን ስትመኝ ።
ተጫውተህ ነበረ በወታደር ካርታ ፣
ይሰጡኛል ብለህ ልትቀፍል ጋኞታ ።
እነሱም ነቁብህ ኣቋም እንደሌለህ ፣
እሜዳ ጥለውህ ደግሞ እንዳልበረደህ ።
አሁንም አማረህ ወይ ልትጫወት ካርታ ፣
ልትገባ ነው ሸገር ሰማሁኝ ሹክሹክታ ።
እንዴትስ ይዋሻል መቃብር ጫፍ ቆሞ ፣
ህሊና ልሳኑን ሁሉን ነገር ታሞ ።
ብለህ አልነበር ወይ በሶስት ወር ሸገር ፣
አሁን ገና ገባኝ ለካስ በጓሮ በር እንደዚህ ልትበር ።
ቀብድ የበላህበት ከሦስት ዓመት በፊት ፣
ሆኖብህ የቀረ ሁሉ ነገር ወረት ።
ልታስበላው ነው ወይ ልትሆንበት ጮሌ ፣
የአርባ ዓመት ወታደር መስሎህ ያንተ ሎሌ ።
መቀመጥ መጨለጥ ይሆን ወይ ስራህ ፣
እኔስ ግራ ገባኝ ብዙም ታዘብኩህ ፣
አቋምም የሌለህ ፍፁም ደሃ ነህ ፣
መቀባጠር በዝቶ ስንቱን ለፍልፈህ ።
ምንድነው ነገሩ የምን መፈርጠጥ ነው ፣
ይሄ ሁሉ ጉራ ለካስ ለወንበር ነው ።
ነበር በአንተ ግዜ ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ ፣
ጭራሽ አይዋሽም እድሜ እንኳን ሲገፋ ።
አንተና መሰሎችህ ልትመሩት መርጧችሁ ፣
ይኸው ተጫወቱ ላጥ ላጥ ብላችሁ ።

መታሰቢያነቱ የውጭው አለም ብርድ ከትግሉ ሜዳ ላስፈነጠራቸው
ለኦቦ ሌንጮ መሸኛ ይሁንልኝ ።
ሜይ 2018
ስቶክሆልም