ኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት የሌለባትና ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ መግባት ብዙ ችግር ያለበት መሆኑ ተገለፀ

አባይ ሚዲያ ዜና
 አቤኔዘር አህመድ

የፕሬስ ነፃነትና የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ በዶች ቬሌ አካዳሚ የማስተማሪያና ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ ውይይት መደረጉን ዶች ቬሌ ዘገበ።

በማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ በሚገኙ ተማሪዎች በተዘጋጀው ውይይት ላይ ኢትዮጵያ በቅርቡ ጋዜጠኞችንና የፖለቲካ እስረኞችን ከእስር ብትለቅም አለም አቀፍ ትልልቅ ተቋማት የሚያወጡት መረጃዎች እንደሚያሳዩትና በውይይቱ ላይ እንደቀረበው  ኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት የሌለባት አገር ተብላ መቀመጧ ተገልጿል።

ስለ ኢትዮጵያ አጠቃላይ ነገሮችና አሁን ያለችበት ደረጃ ምን እንደሚመስል ፡ ስለ ፀረ ሽብር ህጉ ፡ በኢትዮጵያ ያለው ነባራዊ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ምን ይመስላል የሚሉ ነጥቦች በመነሻነት ቀርቦ ውይይት መደረጉ ታውቋል።

በውይይቱ ላይ ከአፍሪካ በፕሬስ ነፃነት ከማይታሙ አገሮች መካከል ከኬኒያ፡ ከደቡብ አፍሪካ እና ከናይጄሪያ የተወከሉ ተማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን የፕሬስ ነፃነት ችግር አለባቸው ከሚባሉት አገራት ከሶሪያ፡ ከግብፅ፡ ከዩክሬን እና ጆርጂያ የተወከሉ ተማሪዎች የአገራቸውን ተሞክሮ ከኢትዮጵያ ጋር እያነፃፀሩ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ላይ ከተነሱት ነጥቦች አንዱ ሬዲዮ በድምፅ መታፈን ሲሆን በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ተማሪዎች በድሮ ታሪካቸው መፅሃፍ ላይ በማንበብ የሚያውቁት መሆኑን ገልፀው ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ዘመን መኖሩ እንግዳ ነገር እንደሆነባቸውና የዶች ቬሌ የአማርኛው ስርጭት ክፍል በኢትዮጵያ መንግስት የድምፅ መታፈን እንደሚፈፀምበት በውይይቱ ላይ ተነስቷል።

ከደቡብ አፍሪካ የተወከለው ተማሪ ከአፓርታይድ በኋላ የገቡበትን የፕሬስ ነፃነት አውድ አንስቶ የኢትዮጵያ መንግስት ነፃ የሆነ ሚዲያ ለመመስረት ምን ያህል ጊዜ ይወስድበታል? ለምንስ ይህን ያህል ጊዜ ወሰደበት? በማለት ጥያቄ አቅርቧል።

ከናይጄሪያ የተወከለው ተማሪ በበኩሉ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ውስጥ አለመውደቋን አንስቶ እንዴት ነው የራሳችሁ የሆነ ነፃ ሚዲያ የሌላችሁ? እኛ ከእናንተ በኋላ የመጣን አገር ነን፡ እናም እንዴት እንዲህ ሊፈጠር ቻለ? የሚል ጥያቄ አንስቶ እንደነበረ ተዘግቧል።

በኢትዮጵያ ሚዲያዎች ነፃ እንዳልወጡና አፋኝ ህጎች ውስጥ አንዱ የፀረ ሽብር ህግ በጋዜጠኞች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እና ከዚህ ህግ ጋር በተያያዘ ብዙ ጋዜጠኞች እንደሚታሰሩ ውይይት ተደርጎበታል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ መግባት ብዙ ችግር ያለበት ፡ ብዙ መስዋእትነት ያለበት ፡ በቀላሉ መረጃ የማይገኝበት መሆኑን በውይይቱ የተነሳ ሲሆን ማህበራዊ ሚዲያን ለመጠቀም ኢንተርኔት በየጊዜው ስለሚዘጋ በአግባቡ መጠቀም የማይቻል መሆኑ ሲገለፅ በውይይቱ የተሳተፉትን ያስገረመ ነበር።