የጉምሩክ ባለስልጣን የነበሩት አቶ መላኩ ፈንታን ጨምሮ ሌሎች ባለሃብቶች ክሳቸው እንዲቋረጥ ትእዛዝ ተሰጠ

አባይ ሚዲያ ዜና

የገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣንን ሲመሩ የነበሩት እና በአገዛዙ በሙስና ክስ ቀርቦባቸው በእስር የቆዩት አቶ መላኩ ፈንታ የቀረበባቸው ክስ እንደሚቋረጥ ተገለጸ።

ከአቶ መላኩ ፈንታ በተጨማሪ የጉምሩክን መስሪያ ቤት በምክትል ዳይሬክተርነት ሲያገለግሉ የነበሩትና ተመሳሳይ ክስ ቀርቦባቸው ለእስር ተዳርገው በቆዩት በአቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ የቀረበው ክስም እንደሚቋረጥ ተዘግቧል።

የፌደራሉ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት አቃቤ ህጉ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሰልጣን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር  በአቶ መላኩ ፈንታ ያቀረበው ክስ እንዲያቋርጥ በላከው ደብዳቤ ጠይቋል።  

ለአዲስ አባባ ማረሚያ ቤት ቃሊቲ በተላከው በዚሁ ደብዳቤ የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ አቶ መላኩ ፈንታን በሌላ ክስ የማይፈልጋቸው ካልሆነ በዛሬው እለት ተከሳሹን ከእስር እንዲለቃቸው እና ነጻ እንዲሆኑ ትእዛዝ ሰጥቷል።  

ከእነ አቶ መላኩ ፈንታ በተጨማሪ በአገዛዙ ክስ ቀርቦባቸው በእስር ላይ የሚገኙ በርካታ ባለሃብቶች ክሳቸው እንደሚቋረጥ እና ከእስር እንደሚለቀቁ ዘገባዎች አመልክተዋል። 

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቤተመንግስት የትግራይ ተወላጆችን በመሰብሰብ ባደረጉት ውይይት በእስር ያሉ ባለሃብቶች እንደሚፈቱ በመጠቆም የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እስራት  ከመጀመሪያው ትክክል እንዳልነበረ እና በሚቀጥሉት ቀናት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንደሚፈቱ መግለጻቸው መዘገቡ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ ምድር ነጻነት እና ፍትህ እንዲሰፍን ከፍተኛ መስዋት እየከፈሉ ያሉት የግንቦት ሰባት የቀድሞው ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን አገዛዙ በማሰሩ ምክንያት ኢትዮጵያ ከምእራብያውያኑ በተለይም ከብርታኒያ ልታገኘው የሚገባትን በርካታ ቢሊየን ዶላር ልታጣ መገደዷን ጠቅላይ ሚንስትሩ በቤተ መንግስቱ ለተሰበሰቡት የትግራይ ተወላጅ ባለስልጣናት እና ባለሃብቶች እውነታውን አፍርጠው መናገራቸው ይታወሳል።