የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው የግንቦት ሰባት አመራር አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ነጻ ወጡ

አባይ ሚዲያ ዜና

የሞት ቅጣት ፍርድ በሌሉበት የተወሰነባቸው እና የአለም አቀፍ ህግን በጣሰ መልኩ ከየመን ሰንአ አየር ማረፊያ ታፍነው ለኢትዮጵያ መንግስት የተላለፉት የነጻነት ታጋዩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር ነጻ ወጡ።

ነጻነትን፣ ፍትህን እንዲሁም የሰለጠኑት አገራት የሚኩራሩበትን የዲሞክራሲ ስርአትን በኢትዮጵያ ምድር ለመገንባት ቤተሰባቸውን እና የተደላደለ ህይወታቸውን ጥለው በበርሃ ትግልን የመረጡት አርበኛ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከ አራት አመታት እስራት በኋላ ነጻ ሊወጡ ችለዋል።

ኢትዮጵያን ከተጫነባት የአገዛዝ ቀምበር ነጻ ለማውጣት እየተንቀሳቀሰ ያለውን የግንቦት ሰባት ድርጅትን በዋና ጸሃፊነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በ 2002 ዓ.ም በሌሉበት የሞት ቅጣት ፍርድ እንደተወሰነባቸው ይታወሳል።

የብርቴን ዜግነት ያላቸው እና የሶስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ ኤሌትሪካል ኢንጅነሪግ በለንደን ከሚገኘው ግሪንዊች ዪኒቨርስቲ ደግሞ ፍልስፍና ያጠኑ ሲሆኑ በለንደን ያለውን የተደላደለ ህይወታቸውን ጥለው ለኢትዮጵያ ነጻነት በርሃ የወረዱ የኢትዮጵያ ባለውለታ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት በጦርነት እና በበሽታ እየወዳደመች ያለችው የመን በ2006 ዓም በሰንአ አየር ማረፊያ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በማፈን ለኢትዮጵያ መንግስት አሳልፋ ከሰጠችበት ጊዜ ጀምሮ የነጻነት ተምሳሌቱ አቶ አንዳርጋቸው በእስር ቤት መራራ ስቃይ እና መከራ ሲፈራረቅባቸው እንደነበረ በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በእስር ቆይታቸው እንቅልፍ እንዳያገኙ እየተደረገ እንደሆነ እና በእስር ቤቱም በአገዛዙ ቶርች እየተደረጉ እንደሆነ የተባበሩት መንግስት በመግለጽ ግልጽ ደብዳቤም ለብርቴን መንግስት እንዲሁም ለኢትዮጵያ አገዛዝም ማስገባቱ  ይታወሳል።

በፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ የነጻነት ታጋዩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ከእስር እንዲፈቱ የዲፕሎማሲያዊና በሰሜኑ የአገሩቷ ክፍል ተደጋጋሚ የሃይል እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱ ይታወሳል።

የሶስቱ ልጆቿቸው እናት እንዲሁም የትዳር አጋራቸው ወይዘሮ የምስራች ሃይለማርያም ባለቤታቸው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከየመን መታፈናቸው ከተሰማበት ሰአት ጀምሮ ተስፋ ባለመቁረጥ የፍትህ  እና የነጻነቱን ታጋይ ከእስር እንዲለቀቅ የሚደነቅ አለም አቀፋዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ የአለም ግዙፍ የዜና አውታሮችን አስደምማለች።

በግንቦት 5 ቀን 2010ዓም አቶ አንዳርጋቸውን ለማሰብ በመዲናዋ በአዲስ አበባ የሰማያዊ ፓርቲ ልዩ ዝግጅት በማዘጋጀት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን የኢትዮጵያ ማንዴላ፣ የነጻነት ተምሳሌት እና አገር ወዳጅ በማለት በስብሰባው የታደሙ ኢትዮጵያውያን ከእስር እንዲወጡ ድምጻቸውን ማሳማታቸው ይታወሳል።

የነጻነት፣ የዲሞክራሲ እና የፍትህ ታጋዩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከአመታት እስራት እና መከራ በኋላ ነጻ በመውጣቷቸው ባለቤታቸው፣ ሶስት ልጆቻቸው፣ እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን እንኳን ደስ አላችሁ በማለት   መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ደስታውን እየገለጸ ይገኛል ።