ዶክተር አብይ አህመድ በሰሜን አሜሪካ የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ለመገኘት ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ ተደረገ

አባይ ሚዲያ ዜና 

በዩናይትድ ስቴትስ ዳላስ ከተማ ለሚዘጋጀው የ2018ቱ የኢትዮጵያውያን የስፖርት ፌስቲቫል ላይ በክብር እንግድነት ለመገኘት ጥያቄ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥያቄያቸው ተቀባይነት ማግኘት እንዳልቻለ ተዘገበ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ዋሽንግተን በሚገኘው በኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል በስፖርት ፌስቲቫሉ ላይ ለመገኘት እና ንግግር ለማደረግ ያቀርቡት ጥያቄ በፌዴሬሽኑ የቦርድ ዳይሬክተር አባላት ውድቅ እንደሆነም ለመረዳት ተችሏል።

በስፖርት ፌስትቫሉ በመገኘት ንግግር ለማድረግ ጠቅላይ ሚንስትሩ ያቀረቡት ጥያቄ የስፖርት ፌስትቫሉ ሊደረግ በተቃረበብበት ወቅት በመሆኑ ምክንያት አስፈላጊውን ለውጥ ለማደርግ የጊዜ ችግር በዋናነት እንደተደነቀረበት ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

ጠቅላይ ሚንስትሩን በዚሁ የስፖርት ፌስቲቫል እንዲገኙ ከኢንሹራንስ ጀምሮ የተለያዩ ወሳኝ ቅድመ ዝግጅቶችን ለማሟላት ፌዴሬሽኑ ያለው ጊዜ በጣም አጭር መሆኑን በማስረዳት በዘንድሮው የስፖርት ውድድር ላይ ዶክተር አብይ አህመድ መገኘት እንደማይችሉ ፌዴሬሽኑ አሳውቋል።

ዶክተር አብይ አህመድ በዘንድሮው ፌስቲቫል ላይ ተገኝተው ንግግር ማድረግ ባይችሉም እንኳን በሰሜን አሜሪካ የስፖርት ፌዴሬሽን በሚያዘጋጀው ፌስቲቫል ላይ ለመገኘት ጥያቄ ያቀረቡ የመጀመሪያው መሪ መሆናቸውን በማሳወቅ በዚህም የቦርዱ ዳይሬክተር አባላት ከፍተኛ ክብር እና ኩራት እንደተሰማቸው ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

በኢትዮጵያ እየተደረጉ ያሉ ማሻሻያዎች  በጎ አዝማሚያን እየጠቆሙ መሆኑን ፌዴሬሽኑ በመግለጽ ዶክተር አብይም በዚሁ የለውጥ ሂደት ላይ እያደረጉ ያለውን ጥረት ፌዴሬሽኑ አድንቋል። ይህ የለውጥና የማሻሻያ እርምጃዎች ሁሉን አቀፍ ሆነው  ኢትዮጵያ ለወደፊቱ ለሁሉም የምትስማማ እንደምትሆን ፌዴሬሽኑ ያለውን ብሩህ ተስፋ አንጸባርቋል።

የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፊዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ በየአመቱ በሚያዘጋጀው የስፖርት ፌስቲቫል በርካታ ኢትዮጵያኖችን በማገናኘት ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅኑበትን መድረክ በምፍጠር ስኬታማነቱን እየቀጠለበት እና እያስመሰከረ እንደሚገኝ ይታወቃል።