አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከ4 አመታት አሰቃቂ እስራት በኋላ ቤተሰቦቻቸውን በአካል ለማግኘት በቅተዋል

አባይ ሚዲያ ዜና

ለነጻነት፣ ለፍትህ፣ እንዲሁም ለዲሞክራሲ በዋጋ ሊተመን የማይችል መስዋትነትን የከፈሉት የግንቦት 7 ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በለንደን ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው።

የኢትዮጵያ ኔልሰን ማንዴላ የሚል ቅጽል ስም የተሰጣቸውን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በርካታ ኢትዮጵያውያን በለንደን ሂትሮ አየር ማረፊያ በመገኘት የጀግና አቀባባለ ያደረጉላቸው ሲሆን የነጻነት ታጋዩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌም ባለቤታቸውን እና ልጆቻቸውንም  ከ 4 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ለማግኘት በቅተዋል።

በብርቴን የሚገኙ ግዙፍ የዜና አውታሮች እና ጋዜጠኞችም በልዩ እና በደመቀ ሁኔታ ኢትዮጵያኖች በአርንጋዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ አላማ ተንቆጥቁጠው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን የተቀበሉበትን ትእይንት በማድነቅ ዘግበዋል።

የሞት ቅጣት ተፈርዶባቸው ለ 4 አመታት በአሰቃቂ ሁኔታ ታስረው በነበሩበት ወቅት ከእስር እንዲለቀቁ የተለያዩ የቅስቀሳ ዘመቻዎችን በማድረግ ለታገሉ ሁሉ ምስጋናቸውን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አስተላልፈዋል።

እሳቸው ለ 4 አመታት በእስር ላይ በነበሩበት ወቅት ልጆቻቸው የከፈሉት ዋጋ እጅግ በጣም ከባድ እንደነበረም አቶ አንዳርጋቸው ተናግረዋል።

ከየመን ሰንአ አየር ማረፊያ የአለም አቀፍ ህግን በሚጻረር መልኩ ታፍነው ለኢትዮጵያ ደህንነት አካላት ተላልፈው የተሰጡት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር ሲፈቱ በአዲስ አበባ እጅግ ደማቅ የሆነ አቀባበል ህዝቡ እንዳደረገላቸው ይታወሳል።

አራት አመታት መታሰራቸው አላማቸው ከሚጠይቀው መስዋትነት ጋር ሲነጻጻር በጣም ትንሽ እንደነበረም በአዲስ አበባ እሳቸውን ለመቀበል ለወጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን በመግለጽ የኢትዮጵያ ህዝብ መብት እስከሚከበር ድረስ ትግላቸውን እንደማያቋርጡ አረጋግጠዋል።

በጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ግብዛ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በቤተ መንግስት በመገኘት ከዶክተር አብይ አህመድ ጋር ለሰአታት የቆየ ውይይት ማድረጋቸው እና ውይይቱም ጥሩ እንደነበር አቶ አንዳርጋቸው መግለጻቸው ይታወቃል።

የብርቴን ጠቅላይ ሚንስትር ወ/ሮ ቴሪዛ ሜይ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ከእስር እንዲለቀቁ በመወሰናቸው ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድን ማመስገናቸውም ተዘግቧል።