ኢትዮጵያውያን በጀርመን ሙኒክ ከተማ በመሰባሰብ ደማቅ ፕሮግራም አደረጉ

አባይ ሚዲያ ዜና

በጀርመን ሙኒክ ከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአገራችንን ባህል ለማስተዋወቅ እንዲሁም ህብረታቸውን ለማጠናከር በማሰብ የተሳካ ፕሮግራም አደረጉ።

በዚህ ፕሮግራም ላይ በርካታ ጀርመናዊውያን እና የሌሎች አገራት ዜጎችም የታደሙ ሲሆን አገራችን ኢትዮጵያ ያላትን አኩሪ ታሪክ፣ ባህል እና መልካም ገጽታ ለታደሙት የውጭ አገር ዜጎች ለማስተዋወቅ ጥረት ተደርጓል።

የኢትዮጵያን ባህል፣ ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሰራሽ ድንቅ ቅርጾቻችንን ለጀርመኖቹ ለማስተዋውቅ  በሙኒክ ከተማ የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ መንበረ ብርሃን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በዚህ ፕሮግራም ላይ  ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገች ለመረዳት ችለናል። ቤተ ክርስቲያኑዋ የኢትዮጵያን ባህል እና ቅርጽ የሚያስረዱ በጀርመንኛ ቋንቋ የተዘጋጁ  በራሪ ወረቀቶችን በብዛት በማሳተም በሙኒክ ከተማ እንዲሰራጭ በማድረግ የኢትዮጵያ አገራችንን አኩሪ ገጽታዎች ለማስተዋወቅ ጥረት አድርጋለች።

የቱሪስት መስህብ በሆነችው በሙኒክ ከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያኖች ቅዳሜ እና እሁድ ባዘጋጁት በዚህ የመሰባሰብ ፕርግራም ላይ በርካታ ጀርመናውያን እንዲሁም የሌሎች አገራት ዜጎች በመገኘት የኢትዮጵያን ባህል እና ሙዚቃ በከፍተኛ አድናቆት ተከታትለዋል።

በነጻነት ታጋዩ በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር ነጻ መውጣት የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ በሙኒክ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባሳለፍነው ማክሰኞ ምሽት ደመቅ ያለ ዝግጅት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያውያን ያዘጋጁት የሁለት ቀናት ፕሮግራም በዋናነት ኢትዮጵያዊነትን በማጎልበት ማህበራዊነትን ለማጠናከር እና ባህልን ለማስተዋወቅ የታቀደ እንደሆነ የፕሮግራሙ አዘጋጅ ኮሜቴ አባል ለአባይ ሚዲያ ገልጸዋል።