ከቤኒሻንጉል ጉምዝ የተፈናቀሉ የአማራ ብሔር ተወላጆች ለ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አቤቱታ ለማቅረብ ወኪል ላኩ

አባይ ሚዲያ ዜና
አቢሰሎም ፍሰሃ
ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ከማሺ ዞን ተፈናቅለን በባህር ዳር ከተማ ምግብ ዋስትና ጊቢ መጋዘን ውስጥ የምንገኝ በቁጥር 527 የምንሆን አባወራ ብቻ ቤተሰብን ሳይጨምር ታግተን እንገኛለን ሲሉ በወኪሎቻቸው በአቶ አበባው ጌትነት፣ በአቶ ቄስ ምናለ አያሌው እና በአቶ ልመንህ መኩሪያ አቤቱታቸውን ለጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ለማቅረብ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
 
አመልካቾቹ ከ1992 ዓ.ም ጀምረው እስከ 2010 በክልሉ መኖራቸውን ገልፀው በኖሩባቸው አመታት ውስጥ ከ5 ጊዜ በላይ በህይወታቸውና በንብረታቸው ላይ ከፈተኛ ጥቃት ሲደርስባቸው መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
 
በ2003 ዓ.ም በድጋሚ በላባችን ያፈራነው ሃብት ተዘርፎ፣ ንብረታችን ተቃጥሎ ተባረን በቡሬ ወረዳ ሰፍረን ከቆየን በኋላ የአማራ ክልል መንግስት ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መንግስት ጋር በመነጋገር ወደዛው ተመልሰን እንድንቀመጥ ተደርጎ ነበር፡፡
 
ጥቅምት 17 2010 ዓ.ም በድጋሚ ምክንያቱን ባላወቅነው ጉዳይ የጎሳ ግጭት በማንሳት በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳትና ውድመት የተፈፀመብን ሲሆን፤ጉዳቱን ለመጥቀስ ያህል 13 ሰዎች ሲገደሉ ከሟቾቹ መካከል የ4ቱ አስክሬን የውሃ ጉድጓድ ውስጥ በመጣሉ ሊገኝ አልቻለም በተጨማሪ በቀስትና በጦር የተወጉትን ጨምሮ ቁጥራቸው 49 የሚሆኑ ሰዎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው፡፡ 149 ቤቶች ከነሙሉ ንብረታቸው በእሳት እንዲወድሙ ሲደረግ ከቁም ከብት ጀምሮ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ተዘርፈዋል፡፡ በአጠቃላይ የወደመውና የጠፋው ንብረት ግምት ድምር ብር 23 000 000 (ሃያ ሶስት ሚሊዮን ብር) መhሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
እኛ በደሉ ከደረሰብን ቀን ጀምረን ቦታውን በመልቀቅ ወደ ክልላችን መግባታችን ቢታወቅም የአማራ ክልል መንግስት በክልሉ የምግብ ዋስትና ጊቢ ውስጥ ፈሰን እያየን አቤቱታችንን ሳይቀበል ቸል በማለት «እናንተ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ነዋሪዎች እንጂ የእኔ ህዝቦች አይደላችሁም ስለዚህ ሄዳችሁ የቤንሻንጉል ጉምዝን ክልል ጠይቁ» በማለት ባለመቀበላቸው በርሃብና በጥማት ዝናብ ላይ ወድቀን እየተሰቃየን እንገኛለን ስለዚህ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ ጉዳያችንን በማየት የወደቅንበትን ቦታና የጠፋብንን ንብረቶች ከግምት ውስጥ በመክተት አፋጣኝ የሆነ መፍትሄ እንዲሰጡን ስንል በትህትና እንጠይቃለን ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁንም አማሮች ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልሎች በመፈናቀል ላይ ይገኛሉ፡፡