እንደሌላው ኢትዮጵያዊ የድሬዳዋ ህዝብም ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በሚጋራው ህገመንግስት ና በራሱ በድሬዳዋ ቻርተር በህግ የተሰጡት መብቶች አሉት ። እነዚህ መብቶች በድሬዳዋ ለሚኖር በሙሉ ያለአድሎ የተሰጡ መብቶች ናቸው ። ለምሳሌ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 41. ቁጥር 3 ላይ “የኢትዮጵያ ዜጎች ሁሉ በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብት አላቸው ።” ሲል ደንግጓል ። በዚህ ህግ ውስጥ ለአንዱ ዜጋ 40% የመጠቀም መብት ለሌላው 20% የሚል ነገር የለውም። በግልፅ እንደምናየው ሁሉም ዜጐች ያለአድልዎ ና መድሎ አገልግሎቱን እንደሚያገኙ ነው የሚደነግገው ።

በድሬዳዋ ቻርተር ተራ ቁጥር 6. ሐ ላይ ደግሞ “ነዋሪዎች (ብሄሮች አይልም ) የከተማው አስተዳደር የሚሰጠውን አገልግሎት በእኩልነት ፣በግልፅነትና በፍትሐዊነት የማግኘት መብት አላቸው ” ይላል ። በዚህም ዜጎች በእኩልነት የማግኘት መብት እንዳላቸው በግልፅ ደንግጓል ።

በጉልት የሚተዳደሩ እናቶችን የሚያፈናቅል ህግ!

ህጎች ከላይ በተገለፀው መሰረት ዜጎች በእኩልነት ና በፍትሃዊነት እንዲሁም በግልፅ አገልግሎቶችን የማግኘት መብት ቢሰጣቸውም በድሬዳዋ ተጨባጭ ሁኔታ ግለሰቦች የህጎቹ የበላይ ሁነው በዜጎቹ መካከል ልዩነትና አድሎ እንዲፈጠር አድርገዋል ። 40፣ 40 ፣ 20 እነዚህን የእኩልነት ና የፍትሃዊነት ህገመንግሥታዊ መብቶችን በመሻር የወሰኑት ውሳኔ ነው ። ይሄ የቁጥር ቀመር የዜጐችን የእኩልነት መብት የነጠቀ ፣ ዜጎች በተወለዱበት ና በአደጉበት ከተማ መስራት እንዳይችሉ ያደረገ የጭቆና መርህ ነው ። በመሆኑም ህገመንግስቱ ና ቻርተሩ የሰጠንን መብት ልትመልሱልን ይገባል ። ከ2000 ዓም ጀምሮ ድሬዳዋ ላይ በመንግሥት መስርያቤት ለመቀጠር ይሄ ፎርሙላ ተግባር ላይ በመዋሉ ምክንያት በርካታ ተወላጆቿ አገር ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል ። የ40፣40፣20 ፎርሙላ ቀስ በቀስ አሁን እስካለንበት የጉልበት ና የጉልት ስራዎችን ፣ ለጥቃቅን አነስተኛ ንግዶች የሚያገለግሉ ማእከላትን ለማከፋፈል ጥቅም ላይ ወደ መዋል ደርሷል ። ከዚህ በሗል ሽንኩርትና ቲማቲም ሸጠው በመጦሪያቸው ጊዜ ስራ አጥ የሆኑ ልጆቻቸውን የሚጦሩ እናቶችም አገር ጥለው መሰደዳቸው ነው ። እነዚህ ግለሰቦች የጫኑብንን የአግላይነት ቀንበር በአንድነትና በህብረት ታግለን አሽቀንጥረን ካልጣልን ድሬድዋዊነታችን ታሪክ ሆኖ መቅረቱ ነው ።

ሁሉም የሚጠቀመው በእኩልነት ብቻ ነው!

የ40፣40፣20 ቀመር ሁሉም የሚከስርበት ቀመር ነው። በኢፍትሃዊነት ና በአድሎ ተጠቃሚነት የለም ። የኦሮሞ ና የሱማሌ ወንድሞቻችን ጥቂቶች በስማቸው ነግደው አተረፉ እንጅ ህዝቡ የተጠቀመው ነገር የለም ። የኦሮሞ ና የሱማሌ ህዝብ የሚጠቀመው በእኩልነትና በፍትሃዊነት እንጅ ሌላውን ወንድሙን በሚያገል የቁጥር ፖለቲካ አይደለም ።ህዝቡ በዚህ ቀመር ቢጠቀም ኖሩ ገና 15 አመት ያልሞላቸው ህፃናት ለስደት አይዳረጉም ነበር ። በአድሎ ህዝቡ ቢጠቀም ኑሮ ገና ሩጠው ያልጠገቡ የኦሮሞ ና የሱማሌ ህፃናት ሴቶች ለአረብ ሃገር ግርድና ባልተዳረጉ ነበር ። መጠቀም የሚቻለው በእኩልነትና በፍትህ መሆኑን አውቀን ድሬዳዋውያን በአንድነት በመቆም ይሄን የአፓርታይድ ህግ ልናስወግደው ይገባል ። ድል ለድሬያችን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here