ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ ዛሬ የተለያዩ ሹም ሽሮችን አደረጉ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ሱራፌል አስራት

አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ ዛሬ የመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዡር ሹም የሆኑትን ጀነራል ሳሞራ የኑስን ከስልጣናቸው በማንሳት በምትካቸውም ጀነራል ሳእረ መኮንን ተክተዋል። ከዚህም በተጨማሪ  ዶ/ር አብይ በብዙወች ዘንድ ጠንካራውና ሀያሉ ሰው በመባል የሚታወቁትን የኢትዮጵያ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የነበሩትን አቶ ጌታቸው አሰፋ በማውረድ በምትካቸው ጄኔራል አደም መሐመድን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በማድረግ ሹመዋቸዋል። ዛሬ በቤተመንግስት በተካሄደው የመሸኛ ዝግጅት ጀነራል ሳሞራ የኑስ በጡረታ ሲሰናበቱ የመረጃና ደህንነት ሹም የነበሩት አቶ ጌታቸው አሰፋ ግን እጣ ፈንታቸው እስከአሁን ድረስ አልታወቀም።

በተያያዘ ዜናም ከአሁን በፊት ከመከላከያ ሰራዊት ታግደው የነበሩትን ሜጀር ጄኔራል አለምሸት ደግፌ እና ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ የነበራቸው ወታደራዊ ማዕረግና ደረጃ ተጠብቆላቸው በጡረታ ከመከላከያ ሰራዊቱ እንዲሰናበቱ መወሰኑ ታውቋል። በሌላ በኩል የቀድሞው የፓርላማ አፈ ጉባኤና የጠ/ሚ የሀገር ደህንነት አማካሪ የነበሩት አባ ዱላ ገመዳና በአሜሪካን ሀገር የኢትዮጵያ አንባሳደር የነበሩት አቶ ግርማ ብሩ በጡረታ መሰናበታቸው ታውቋል።