ምነው ደም ደም አይለን (በላይነህ አባተ)

0

ፍትህ ሳያደርቀው የፈሰሰን ፍዳ፣

ንስሀ ሳያጥበው የቆሸሸን ጓዳ፣

ዱለትን መቋደስ ከገዳዮች ጋራ፣

የሐጥያትም ሐጥያት የታሪክም ዕዳ!

ፍትህ ነፃነትን መብትን ተርበው፣

ኢፍታዊነትን እንደ አውሬ ተናንቀው፣

ስንቶቹ ተሰው ባሩድ ተመግበው?

ነፃነት ወይም ሞት በቃ ዘራፍ ብለው፣

ስንቶች ተሰውልን ጫካ ዱር ሸፍተው?

በእሬቻ በጥምቀት በመስጊድ ሰገዳው፣

በሰፈር መንደሩ በገጠር ከተማው፣

እንደ ፋሲካ በግ የታረደ ስንት ነው?

ባዶ ስድስት ጉድጓድ በጪስ የታፈነው፣

ቃሊቲ ዓለም በቃኝ የተዘቀዘቀው፣

ቅሊንጦና ዝዋይ በእሳት የነደደው፣

ሽሮሜዳ ታስሮ ጥፍሩ የወለቀው፣

ብር ሸለቆ አዘዞ ጉረኖ የገባው፣

ማሰቃያ ቦታው ጭራሽ ያልታወቀው፣

ስንት መከረኛ ምን ያህል ዜጋ ነው?

የጋንቤላን ምድር ሽፍን ያደረገው፣

ኦጋዴን በርሃን በጎርፍ የጠረገው፣

ምን ያህል ሬሳ ስንት በርሜል ደም ነው?

ጎንደር ደብረታቦር በባሩድ ያለቀው፣

ባህርዳር ወልድያ ስናይፐር የፈጀው፣

አምቦ ደብረ ዘይት ጥይት ያረገፈው፣

መች ተቆጥሮ ያልቃል ቆጣሪ ቢኖረው?

በሽሽት በስደት በአውሬ የተበላው፣

ባህርን ሲሻገር ድንብልዝ ያሰመጠው፣

ምን ያህል ኮረዳ ምን ያህል ጎበዝ ነው?

ወልቃይት ራያ ዘሩ የመከነው፣

በደኖ በገደል የተወረወረው፣

አሶሳ መተከል የተቆራረጠው፣

ከፋ ኢሉባቦር ሜጫ የከተፈው፣

አይምሯችን ያስላ ምን ያህል ሕዝብ ነው?

ይኸ ግፍ ሲፈጠም ለካስ ያለቀስነው፣

እርሾና አብሲት ጥለን በትኩስ ደማቸው፣

በተሰውት አጥንት ዳቦ ልንጋግር ነው፡፡

ጅቦቹ ሰው በሉ ስንል የነበረው፣

ለካስ የውሻ ጠጉር ካባ ደርበን ነው፣

ትርፍራፊ ልፋጭ መጎተት አምሮን ነው፡፡

በየ አደባባዩ ስንጮህ የነበርነው፣

ለካስ በሙታን ደም ገንፎ ልንሰራ ነው፡፡

አይ ጊዜ ፈታኙ አይ ጊዜ መስካሪው፣

ስንቱን አጭበርባሪ ከርሳም አጋለጥከው፡፡

በእርቅና በሰላም እያመካኘ፣

ስንቱ ይሁዳ ሰው ለሰይጣን ሰገደ፡፡

ዓለም ፍርደ-ገምድል ዓለም ወለወልዳ፣

ቀጣፊን አጽዳቂ ሐቀኛን ኮንና፡፡

በእርቅና በሰላም ስንት ሆዳም ነገደ፣

የሰማእት እሬሳ እየተራመደ፡፡

የሰማእት ሥጋ ቅርጫ ለመቃረጥ፣

በሙታንም አጥንት ንግድ ቤት ለመክፈት፣

ከገዳዮች ጋራ አብረን ስንዶልት፣

ምነው ደም ደም አይለን? ምነው አይለን ስቅጥጥ?

ገዳይ ችሎት ሳይቀርብ ሟችም ሳያገኝ ፍርድ፣

ፍትህ ገደል ገብታ ንስሃ እንጦሮጦስ፣

እርምን ልንጠሸቅም ከገዳይ ስንቀርብ ማድ፣

ምነው ደም ደም አይለን? ምነው አይሰቀጥጥ?

ሥጋውን እንጀራ ደሙንም ሰርተን ወጥ፣

እየሸመለልን ሰማእት ልንውጥ፣

ከነፍሰ በላዎች አብረን ስንቀመጥ፣

ምነው ደም ደም አይለን? ምነው አይለን ስቅጥጥ?

ይገርማል! ሰው ከንቱ!

በላይነህ አባተ ([email protected])

ሰኔ ሁለት ሺ አስር ዓ.ም.