የዶክተር አቢይና የዊኒስተን ቸርችል ፈታኝ ውሳኔዎች (በሙሴ ማሞ ተስፋዬ)

0

ክላይን ሶኖግራስ የተሰኘው ጸሐፊ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚንስቴር ዊኒስተን ቸርችል ያጋጠማቸውን አጣብቂኝና ፈታኝ ውሳኔ “መንታ እውነቶች” በተሰኘው መጣጥፉ እንዲህ ያስታውሰዋል። “የእንግሊዝ የመረጃ ሰራተኞች ከብዙ ልፋትና ሙከራ በኋላ የጀርመን መልእክት መላላኪያ የሚስጥር ጥብቅ ኮድ ደረሱበት። በመጀመሪያ የጠለፉትም መልእክት የጀርመን አየር ሀይል እንግሊዝ አገር “ኮመንተሪ” የተባለውን ቦታ በአየር እንደሚደበድብ የሚያመላክት ነበረ። ይህ ሚስጥር እንግሊዞች ከደረሱበት በኋላ ምን ያድርጉ? እንግሊዞች በዛ አካባቢ ያሉትን ነዋሪዎች በአስቸኳይ ወደ ሌላ ቦታ ቢያሸሹ ጀርመኖች የሚስጥር መላላኪያው ኮድ በእንግሊዞች እንደተደረሰበት ይነቃሉ። የሚስጥር መላላኪያቸውንም ቀይረው የበለጠ ጥብቅ ያደርጉታል።እንግሊዞችም እጅግ አስፈላጊ መረጃዎችን ከማግኘት ይቀራሉ። እንግሊዞች ይህ መረጃ ደርሶዋቸው ሰላማዊውን ህዝብ ከዛ ቦታ በአስቸኳይ ካላሸሹ ብዙ ንጹህ ህዝብ ያልቃል። ከዊንስተን ቸርችል በታች ያሉት ይህንን መወሠን ስላቃታቸው ውሳኔው ዊንስተን ቸርችል ጫንቃ ላይ ወደቀ። ዊኒስተን ቸርችልም አመዛዝነው የሚስጥር ኮዱ እንደተደረሰበት ከሚታወቅ እነዛ ሰዎች መሞታቸውን መረጡ። ብዙ የታሪክ ሊቆች እንደሚስማሙበት ዊንስተን ቸርችል ያንን አስጨናቂ ውሳኔ በድፍረት በመወሰናቸው የጀርመን ሽንፈት ታተመ።”

አዎ፤ አንዳንድ መልካም ውሳኔዎች ቀላል አይደሉም። አንዳንድ ውሳኔዎች ንብረት ያወድማሉ፤ ድንበር ያጠባሉ፤ሰው ያስገድላሉ። አንዳንድ ውሳኔዎች አማራጭና አቋራጭ የላቸውም። የግድ ወቅታዊና ቁርጥ ያለ ውሳኔዎችን ይሻሉ። በጊዜው አለመወሰን እንኳን እራሱ ውሳኔ ነው። ዊንስተን ቸርችል ያኔ በኮምንተሪ ያደረጉት ይህንን ነው። ጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድም በባድሜ ጉዳይ ላይ የወሰኑት ተመሳሳዩን ነው።

በአለም ላይ ያሉ ጦርነቶች ሁሉ ተጠቃለው በሁለት ጎራ ይመደባሉ። ባጭሩ አስፈላጊና አላስፈላጊ ጦርነቶች ተብለው። ከዚህም በላይ ጦርነት በቀላሉ መታወጅ የማይገባው፤ አማራጭ የለሽን ግጭት፤ አለመግባባትንና ውዝግብን ማስወገጃ የመጨረሻ እርምጃ መሆን ይኖርበታል። በብዙ መመዘኛዎች የባድመ ጦርነት ከጅምሩ አስፈላጊና አስገዳጅ ካልሆኑ  ጦርነቶች ውስጥ ይካተታሉ ብዬ በግሌ አምናለሁ። የባድመ ጦርነት ዋጋውና ውጤቱ የማይመጣጠን ታሪካዊ ስህተት ነው እላለሁ። አሁንም የዚህን ከጅምሩ አላስፈላጊ የነበረ የብዙ ወጣቶችን ህይወት የቀጠፈ ጦርነት አተላ ሊከተለን አይገባም። ብዙ ህይወትና መዋእለ ንዋይ የተገበረበት የባድሜ ጉዳይ ያበቃለት ያኔ የቀደመው መንግስት ይግባኝ የለሹን የአልጀርስ ድርድር ፈርሞ በተቀበለበት ጊዜ ነበረ። ጠቅላይ ሚንስቴር አቢይ አህመድና መንግስት የወሰኑት ይህንኑ አስፈላጊ የሆነ ከባድና አስቸጋሪ ያበቃለት ውሳኔ እልባት መስጠት ነው።  ለሀገራችንና ለአንድነታችንን በዚህ ጦርነት የተሰዉት ወገኖቻችን የማይተካ ህይወት እያንገበገበን ይህንን ውሳኔ ልናደርግ፤ ልንደግፍ ይገባናል።   

 የመሪዎች አንዱና ታላቁ ሐላፊነት አስገዳጅና አስጨናቂ ውሳኔዎችን መወሰን ነው። በተለይ የመጨረሻው ቁንጮ ላይ ያሉት መሪዎች ለሌሎች ወደ ላይ የሚገፉት ወይም የሚያስተላልፉት ውሳኔ አይኖራቸውም። እሳቸው ዘንድ የሚደርሰው ጉዳይን የግድ ወስነው ሀላፊነቱን መውስድ እንደሚገባቸው የተረዱት 33 ኛው የአሜሪካ ፕሬዜዳንት ሃሪ ትሩማን ”The buck stops here”( የሚንገዋለለው ውሳኔ እዚህ ላይ ያበቃል) የሚል ታዋቂ ጽሁፍ የቢሮ ጠረጴዛቸው ላይ በጉልህ አድርገው ነበረ።  የጠንካራ  መሪዎችም አንዱ መታወቂያ ሲንገዋለል የመጣውን ውሳኔ የሚጠይቅ ነገር ተቀብሎ በጊዜው በድፍረትና በማስተዋል መወሰን ነው። ለእውነተኛና አስተዋይ መሪ አስፈላጊ የሆኑትን አስቸጋሪና አስጨናቂ ውሳኔዎችን አለመወሰን አማራጭ አይደለም። አለአግባቡ ማዘግየትም እራሱ አለመወሰን ነው። አለመወሰን ደግሞ ዞሮዞሮ ያው መወሰን ነው። በቁርጥ ውሳኔአቸው የሚታወቁት ፕሬዜዳንት ሬጋን በወጣትነታቸው የተማሩት ይህንኑ ነበረ።

ሬጋን ገና ወጣት ሳሉ አንድ ሀብላም አክስታቸው ጫማ ሊያሰሩላቸው በጊዜው ወደ ታወቀ ጫማ ሰሪ ዘንድ ወሰዷቸው። ሬጋን እግራቸውን ከተለኩ በኋላ አይነቱንና ቀለሙን መምረጥ አቃታቸው። ጓደኞቻቸው ዘንድ ሄደው ሲያማክሩ ግማሹ ሹል ጫማ ሲላቸው ከፊሉ ደግሞ ክቡን መከራቸው። አንዳንዶቹ ቡኒ ጫማ ሲሉ ሌሎቹ በጥቁሩ ወተወቷቸው። ሬጋን ግራ ተጋብተውና መምረጥ አቅቷቸው ሳይወስኑ ጥቂት ቀናት አለፉ። ይህንን የተረዱት አክስታቸው ወደ ጫማ ሰሪው ዘንድ ሄዱና በሬጋን ፋንታ ወሰኑና ክፍያውን ፈጽመው ተመለሱ። በቀጠሮው ቀን ሬጋን በጉጉት ሲሄዱ አንድ እግሩ ክብና ጥቁር፤ ሌላኛው እግሩ ሹልና ቡኒ ጫማ አገኙ። ሬጋንም በወጣትነታቸው በጊዜው በማስተዋልና በእርጋታ አለመዘግየት የሚደረግ ውሳኔን አስፈላጊነት ተማሩ።

ጠቅላይ ሚንስቴር አቢይ አህመድ ይህንን ታሪካዊ ስህተት ተጋፍጠው መራር የሆነውን ትክክለኛ ውሳኔ መወሰናቸው እንደኔ በአጭር ጊዜ ውስጥ እስካሁን ከሰሯቸው ስራዎች ሁሉ የበለጠ እንዳከብራቸውና፤ እንድደግፋቸውና እንዳደንቃቸውም አስችሎኛል። እንደዚህ አይነት ውሳኔ ከመወሰን በላይ ግን ታላቁ ጥበብ አስቀድሞውኑ አስፈላጊ ያልሆነ ጦርነት ማወጅና ማድረግ ለትውልድ የሚተርፍ ታሪካዊ የሆነ ስህተት መሆኑን መረዳት ነው። አስፈላጊና አላስፈላጊ የሆነን ጦርነት ለይቶ ማወቅ ነው። አስፈላጊና አማራጭ የለሽ አስገዳጅ ጦርንርትንም ማሸነፍ ጀግና ያስብላል። ከዚህ የበለጠው ታላቁ የጦር ጀግና ግን አስቀድሞውኑ አላስፈላጊ ጦርነትን ማስወገድ የቻለ መሪ ነው።

Mussie Mamo Tesfaye

Amen Radio 1120AM New World Radio

Website; www.amenmedia.org  Email; [email protected]

Tel; (703) 589-6473