አማራነት በድሬዳዋ

በአጠቃላይ በሃገራችን አማራነት እንደወንጀል የመታየቱ ጉዳይ አነጋጋሪና እልባት ያልተገኘለት ጉዳይ ነው : ለዚህ ደግሞ ተጠያቂ በደፈናው ኢህአዴግ ሳይሆን ብአዴን ነው:: በዚህ ላይ ማብራሪያ ይሰጥ ከተባለ ቀናቶችና ገፆች አይበቁም::

ይህ ሆኖ እንዳለ በድሬዳዋ የሚኖር የአማራ ተወላጅ ከብአዴን ዕይታ ውጭ ነው:: ብአዴን የድሬዳዋን አማራ አያውቅም : የድሬዳዋም አማራ ብአዴንን መከታ አድርጎ አያውቅም:: በታሪክ እንደተዘገበው የድሬዳዋ አማራ ከሌላ ስፍራ ፈልሶ እንደመጣም የማያሻማ ሃቅ ነው:: ድሬዳዋ ትርጏሜዋ በኦሮምኛ የመድሃኒት ስፍር(ሜዳ) ማለት እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን:: ይህም ማለት ከማንም በፊት የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ድሬዳዋ ይኖሩ ነበር ማለት ነው::

በአሁኑ ሰዓት የድሬዳዋ አማራ የሚባለው እንደማንኛውም የኢትዮጲያ ዜጋ ኑሮን ለማሸነፍ ይሁን በሌላ ምክንያት ጭሮ : ላንጌ: ሂርና ከዛም ሐረርና ድሬዳዋ የፈለሰ ነው:: ይህም በድሬዳዋ ከሰፈረ ከ 100 ዓመታት በላይ ሆኖቷል:: የድሬዳዋ አማራ ሌላ ክልል የለውም : ድሬዳዋ ብቻ ናት::

አብዛኛውን የድሬዳዋ አማራ ስለቅደመ አያቶቹ ቢጠየቅ ወደ አማራ ክልል አይጠቁምም: ይህም የሚያመለክተው ቀደምት አያቶቹ ከሐረርጌ(ጭሮ : ላንጌና ቀርሳ) እንደሆኑ ነው:: ከዛ ያለፈ ዘር መቁጠር የሚችል ያለ አማራ የሚገኝ አይመስለኝም::

የድሬዳዋ አማራ ከአማራ ክልል ይልቅ ከሐረርጌ ኦሮሞ ጋር ተፋቅሮና ተወልዶ እንደኖረ አንዱ ህያው ምስክር እኔ ነኝ:: አያቴ አንድን የኦሮሞ ተወላጅ በሚያስቀና መልኩ ኦሮምኛውን ስታቀላጥፍ ለሰማት የአማራ ዘር ግንድ ያለባት አትመስልም:: አንድንም የድሬዳዋ ኦሮሞ አማርኛ ከነተረትና ምሳሌው : ቅኔንም ሲዘርፍ ለሰማ እንግዳ ድንግርግር ማድረጉ አይቀርም::

ከነዚህ ጊዜያት ወዲህ የድሬዳዋ ተወላጅ ሶማልኛን አደርኛን አልፎ ተርፎ አረብኛን ኧረ እንደውም ፈረንሳይኛንና ኩባኛን የሚናገር መስማት ብርቅ አይደለም:: ይህም በአሁኑ ሰዓት የኦሮሞ ተወላጅ ብልጫውን እንደያዘ ሆኖ የሌሎች ብሔሮችም ስብጥር መሆኗ ከግለሰብ አልፎ ለፌዴራል መንግስቱ ፈተና ሆኖበታል::

ለዚህም ነው የድሬዳዋ ሰው ዘር የለውም የምንለው:: በእያንዳንዱ ቤተሰብ አማራ: ኦሮሞ: ሶማሌ: አደሬ: ከዛም ባለፈ የፈረንጅ ክልስ አይጠፋም:: አያቴ ከመኖሪያ ቤታችንን በፍፁም መልቀቅ አትፈልግም:: ቀባሪዎቼ ጎረቤቶቼ ናቸው ትላለች: ሶማሌና ኦሮሞ:: ከጎረቤታችንም የምሰማው ታሪክ ተመሳሳይ ነው::

አያቶቻችን ይህን የመሰለ አንድነት: ወዳጅነት: ፍቅር ለኛ አስተላልፈዋል:: የአማራነት: የኦሮሞነት : የሶማሌነት : የብሔር ሳይሆን የድሬዳዋነት:: አሁንም ወንድም እህቶቼ የድሬዳዋ ኦሮሞ የሚተዳደረው በኦህዴድ : የሶማሌ ተወላጅ የሚተዳደረው በሶህዴፖ : አማራውም በብአዴን: የድሬዳዋ አደሬ እንኳ በሐረሪ አይደለም: በድሬዳዋ አስተዳደር ነው::

ዛሬ ላይ ሆነን የድሬዳዋ አማራ ቢጮህ ለአማራ ክልል ሳይሆን ለድሬዳዋ ነው:: ይህንንም የድሬዳዋ ኦሮሞ: ሶማሌ: አደሬ: ትግሬ: ጉራጌ ብሔሩን ሳይሆን ከተማውን አስቦ በአንድነት ለድሬዳዋ ከተማ እድገት በህብረት መታገል ይኖርብናል:: እየኖርን ያለነው በድሬዳዋ ስለሆነ: ስንታመም የምንታከመው በድሬዳዋ ስለሆነ: ልጆቻችንን የሚማሩት በደሬዳዋ ስለሆነ: ሽር ብትን የምንልበት መንገድ በድሬዳዋ ስለሆነ: ስራም የምንሰራው በድሬዳዋ ስልሆነ….

ስንወለድም የድሬ ልጅ : ጆሌ ድሬ: እያል ድርዳቤ ነን: ስንሞትም የድሬ ልጅ : ጆሌ ድሬ: እያል ድርዳቤ ነን::

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here