እርቅና ይቅርታ ያስፈልገናል! ከስርነቀልነት ያነሰ ለውጥ አንቀበልም! ሲል እስክንድር ነጋ ተናገረ

0

ትናንት ዕሁድ (በ6/10/2018) በቨርጂኒያ ግዛት አሌክሣንድሪያ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ሒልተን ሆቴል፥ የዲሲ ሜትሮ ነዋሪ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለጀግናው ጋዜጠኛና የመብት አቀንቃኝ የምሥጋና ዝግጅት አድርገው ውለዋል።

እስክንድር በእስካሁኑ ትንቅንቅ እንዳልደከመና በኢትዮጵያ ሙሉ ዲሞክራሢ ሰፍኖ ዜጎቿ ሁሉ ነፃ እስኪሆኑ ድረስ ትግሉ ለደቂቃዎችም ሳያባራ እንደሚቀጥል ገለፀ። እስክንድር መድረኩን ከተረከበ በሁዋላ ሽርፍራፊ ደቂቃዎች እንኩዋን ሳያባክን ነው የአገሩንና ሕዝብዋን ነፃ መሆን ላይ ያዘጋጀውን ፅሁፍ ያቀረበው።

ፅሁፉን ለማዘጋጀት ቀናትን እንደወሰደበት ቢገልፅም የተለያዩ የዓለም ሀገራትን የፖለቲካ ልምዶች በተለይም የደቡብ አፍሪካን ልምድ ተንተርሶ ጥልቅ ትንተና አድርጎዋል። በአዳራሹ የተሰበሰበው ሰው በሙሉ ዐይንና ቀልብ ሙሉ በሙሉ ጀግናው ላይ ያረፈ ቢሆንም፥ የእስክንድር ቀልብና ምናብ ግን አዳራሹን ጥሶ አትላንቲክን ዘሎ እሱ እንዲፈታ ሕይወታቸውን የሰጡ ወጣቶች ዘንድ ነበር።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዕርቅና ይቅርታ እንዲዘጋጅ እስክንድር ጠይቆዋል። ይቅርታና ዕርቅ ሲባል ግፍ የዋሉ በነፃ ይሸኛሉ ግፍ የተዋለባቸውም ከነሕመማቸው ይዘነጋሉ ማለት እንዳልሆነ እስክንድር አብራርቶዋል። ሕዝብ በተሰበሰበበት ሸንጎ የግፍ ዋዮች ተግባር በዝርዝር እንደሚቀርብና ተበዳዮች በይፋ ይቅርታ እንደሚጠየቁ ገልፆ፥ ከስቃያቸው ማገገም ይችሉ ዘንድ አቅም የፈቀደው ካሣ ያገኛሉ ብሎዋል። ያደረሱትን በደል ዘርዝረው ይቅርታ ለመጠየቅ ባልፈቀዱ በዳዮች ላይ በመደበኛ ፍርድ ቤት ክስ ይመሰረታል ሲል ጀግናው አትቶዋል።

እስክንድር እስካሁን በዶ/ር ዓቢይ እየተወሰዱ ያሉትን እርምጃዎች ያወደሰ ሲሆን፥ ለበጎ ሥራዎቻቸው ሁሉ ይደገፉ ዘንድ ተማፅኖዋል። ከእውነተኛ ዲሞክራሢ ግንባታ ፈቀቅ የማለት ዝንባሌ ባሳዩ ግዜ፥ የነፃነት ትግሉ ማንንም ቢሆን የማይታገስ መሆኑን አበክሮ ገልፆዋል።

ለዲምክራሢና ለኢትዮጵያ ነጻነት ሲፈጋ ከደርዘን ጊዜ በላይ ሲታሠር ሲፈታ ለትዳሩ፥ ለቤተሰቡ፥ ለራሡ ፋታ አጥቶ የኖረውን ጀግና፥ ኅብረተሰቡ ካባ አልብሶት ሙሽራዬ እያለ እንደአዲስ ድሮታል። ያደቆነው የነፃነት መንፈሥና የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍቅር ጀግናውን ካአሁንም በሁዋላ ለባለቤቱና ለህፃን ልጁ ፋታ የሰጡት አይመስልም።

አንዲት እናት “ዕግዚዖ ኢትዮጵያ ያፈቀሩሽ ሁሉ ምነው እንዲህ መከራቸው መብዛቱ። እባክህ አምላኬ በቃ በላትና ሰው ሁሉ የሰላም ኑሮውን ይጀምር።” ሲሉ ተደምጠዋል።

(ይህን አስደማሚ ዝግጅት የሚመለከት ሪፖርታዥ ይዘን እንቀርባለን።)