እኔን የከነከነኝ እናንተንም ከከነከናችሁ ልጠይቃችሁ

በነብዩ ተፈራ ለማ

ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ በርካታ ለውጦችን ማየት ችለናል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ዋጋው ጨምሯል፣ አንድ ዜጋ አንድ ነው ተብሎ እንደማይጠቅም ዕቃ መጣሉ ቀርቶ ክብርና ማዕረግ አግኝቷል፤ የፈለጉትን ለማድረግና ያሻን ለመፈፀም በማህበር መሆን በቂ ነው መባሉ ቀርቶ ሁሉም በተናጠል ዋጋም ድምፅም እንዳለው በይፋ ታይቷል፡፡ ይህን ላሳየን ፈጣሪ ምስጋና ይድረሰው፡፡

ባንድ ወቅት በዘመናችን እጅግ ሀብታም ከሚባሉት አንዱ፣ ወደአንድ ድንቅ ኢትዮጵያዊ ቤት በእንግድነት ይሄዳሉ፡፡ ድንቅ ኢትዮጵያዊ የተባሉት ሰው ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ተቀምጠው የሚያስደንቁ ሥራዎችን ለሀገር እየሰሩ የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ ነገር ግን ባለቤታቸው በውርስ ባገኙት ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ነበር የሚኖሩት፡፡ ታዲያ አጅግ ሀብታሙ ሰው ወደባለቤትየዋ ጆሮ ጠጋ ብለው ‹‹ ጋሼ ቤቴን እንዲያይብኝ አልፈልግም፣ እሱ እንዲህ ባለ ቤት ውስጥ እየኖረ እኔ የምኖርበትን ሁኔታ ሳስብ አፍራለሁ›› አሉ፡፡ ይህ የተባለላቸው ሰው የቀድሞ መንገዶች ባስላጣን ዋና ሥራአስኪያጅ የነበሩት ኢንጂነር ፍቃደ ኃይሌ ናቸው፡፡ ዛሬ በሙስና ተጠርጥረሃል በሚል ወሕኒ ከተጣሉ ወደ አንድ አመት እየተጠጋቸው ነው፡፡ እስካሁን ማስረጃም ውሳኔም የለም፡፡

እኚህን ሰው በቅርበት ለማወቅ ዕደሉ ነበረኝ፣ ሀገሬን እንድወድ፣ ትልቅ ትንሽ ሳልል ሁሉንም የሰው ልጅ እንዳከብር፣ ምክንያታዊና ተጠየቃዊ አስተሳሰቤን አንዳዳብር፣ አድልዎና ሌብነት ነውር እንደሆነ ያስተማሩኝ ኢንጂነር ፍቃደ ኃይሌ ናቸው፡፡ ትምህርቱ በቲዎሪ ብቻ አልነበረም በተግባርም ጭምር እንጂ፡፡ ሌላው ቀርቶ ‹‹ ሰዉ ዘመዱን በየቦታው እየሰገሰገ ሲጠቅም አሱ ግን እኛን ወንድሞቹን ሥራ ለማሰቀጠርና ለመጥቀም ፍላጎት የለውም›› ብለው የሚኮንኑዋቸው ዘመዶቻቸውን ጫጫታ ባንድ ወቅት እሰማ ነበር፡፡ እሳቸው ግን የመርሕ ሰው ናቸውና ንቅንቅም አላሉም፡፡ ዛሬ ከጠቅላይ ሚንስትራችን የምሰማቸው፣ የቅንነት፣ የይቅርታ፣ የፍቅርና የመግባባት አስተሳሰቦች ከኢንጂነሩ ስሰማቸው ያደኳቸው ናቸው፡፡ የሀገር ፍቅራቸውና ሚዛናዊ አስተሳሰባቸው ወደር የለውም፡፡ እውነቱን ልንገራችሁ፣ እሳቸው ስራቸውን በተመለከተ የሚጋፈጡ ቁርጠኛ ሰው ቢሆኑም ስልጣንና ፖለቲካን ብዙም አይወዱም እንጂ እኔ ለሀገር መሪነት የምመኛቸው ሰው ነበሩ፡፡ ዛሬ በወሕኒ ተጥለው አስታዋሽ ማጣታቸው፣ በዚያ ላይ ህመማቸው ጠንቶ ምን ያህል እየተጎሳቆሉ እንደሆነ ሳይና ሀገሬ ከማይተኩ ብርቅ ልጆቿ መካከል አንዱን እያጣች እንደሆነ ሳስብ እጅግ አዝናለሁ፡፡

 ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደፍፁም ጠላት ተቆጥረው የሞትፍርድ የተፈረደባቸውን ሳይቀር ሲፈቱ የኢንጂነሩን ዋጋ ምነው እንዲህ አሳነሱት ብዬም እጠይቃለሁ፡፡ ወይስ ፍትህን ለማግኘት ዛሬም የቲፎዞ ብዛትና ጫጫታ ያስፈልግ ይሆን? ብዙዎች ስለሀገር ወዳድነታቸውና ስለሀቀኝነታቸው የሚመሰክሩላቸው ኢንጂነር ፍቃደ ኃይሌ አጥፍተው እንኳ ቢሆን ጥፋታቸው ከነማን በልጦ ነው ምህረት የተነፈጉት?