የሞተልሽ ቀርቶ! ቴዲ አፍሮ ሲጠበቅ ሠራዊት ፍቅሬ መጣ! (ድንበሩ ደግነቱ)

ቢትወደድ አስፍሐ ወልደሚካዔል “ለኤርትራ የመገንጠል እንቅስቃሴ መነሻው የፌዴሬሽኑ መፍረስ ነው።” ተብሎ በሚቀርበው ሙግት ጨርሶ አይስማሙም። ለኃይለሥላሴ የማይናወጥ ታማኝነት እንዳላቸው፥ በደግ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በክፉውም ቀን ያስመሰከሩት እኚህ ሰው፥ ለኤርትራ ችግር ጣታቸውን የሚጠቁሙት በንጉሡ የአስተዳደር ችሎታ ማነስና ውለታ ቢስነት ላይ ነው። ፌዴሬሽኑን በማፍረስ የአንበሳው ድርሻ የሳቸው በመሆኑ፥ ሰው የራሡ ጥፋት ስለማይታየው ሊሆን ይችላል። ቢሆንም የቢትወደድ ክርክር ውሀ ይቁዋጥራል። ንጉሡ ፌዴሬሽኑን ካስፈረሱና ሥልጣናቸውን ካደላደሉ በሁዋላ፥ ለአንድነት ሲፈጉ የኖሩትንና ፌዴሬሽኑን በመናድ ያገዙዋቸውን የኤርትራ ተወላጆች ችላ ብለው፥ በተቃራኒው ከነዚህ ወገኖች ጋር ደም አፋሳሽ ትግል ያደረጉ ራቢጣዎችን በሹመት አንበሸበሹ። የአንድነት ታጋዮቹን ከትላንት የኢትዮጵያ ጠላቶች ትዕዛዝ እንዲቀበሉ አደረጉዋቸው።

ያለርኅራሄ ራቢጣዎችን እየተናነቀ ይደፋ የነበረው የተድላ ዕቁቢትን ውለታ ዘንግተው፥ ለራቢጣው ተስፋዮሐንስ ተገዛ ብለው ፈረዱበት። የተድላ ዕቁቢት ኅሊና ለባንዳ መታዘዝ አቃተውና፥ ከነክብሩ ራሱን በራሱ እስከወዲያኛው ያሰናበተው በወራት ውስጥ ነው። ፀሀዩ ንጉሥ ለሐገር ያበረከቱት ውለታ የማይዘነጋ ቢሆንም፥ የታሪክ ምፀት ሆኖ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሥደተኛ ንጉሥ መሆናቸው አለመታደል ነበር። ከንጉሠ ነገሥታት ሁሉ በልጠው፥ ለረዥም ዘመናት ሥልጣን ላይ ነፍሥ አውቀው፥ ሥልጣን ላይ ያረጁ ቢሆንም፥ ሥደተኛ ያውም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሥደተኛ ንጉሥ መሆናቸው ዕድለ ቢስ አደረጋቸው። ጦሱ አገሪቱን ከማትወጣበት ቅርቃር መክተቱና ለኢትዮጵያውያን የማይድን ቁስል መሆኑ፥ አይጥ በበላ እንዲሉ ያንገበግባል። ኃይለሥላሴ መሠደዳቸው ባንዳና ሥደተኛን በደግ፥ አርበኞችን በጥርጣሬ ዐይን ለማየት ዳረጋቸው። አርበኞች ይህ ቢያንገበግባቸው “ሀገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ!” ብለው ቆዘሙ። ልጆቻቸውም “ጎበዝ ምንድነው መላ?” በማለት ጠይቀው “አይተህ ነው ጊዜን ወደሚያደላ!” ብለው ተሽቀዳድመው ራሳቸው መለሱ። አባቶቻቸው ተከፍተው ሲያነቡ ያዩዋቸው የአንድነት አፍቃሪ የኤርትራ ተወላጆች ልጆች፥ ጠመንጃ ወልውለው ዱር ቤቴ አሉና የአባቶቻቸውን ‘ስህተት’ አረሙት።

‘በእግዚአብሔር የተቀቡልን ናቸው!’ ተብለው በብዙ ታላላቅ ሰዎች እየተነገረላቸው ያሉት ብሩሁና ባለ ቅን ልቡናው መሪያችን፥ ዶ/ር አቢይም፥ የማናውቀውን ግፍና ሰቆቃ ካሳየን፥ ጠይሙን ፋሺስት ከማገልገል ውጪ፥ ለሃያ ሠባት ዓመታት ፋይዳ ካልነበረው ኢሕአደግ መውጣታቸው እንደ ኃይለስላሤ ስደት አለመታደል እንዳይሆን ፈራን። ዶ/ር ዐቢይ ከኢህአደግ መውጣታቸው አድርባይ፥ እበላ ባዮችና የኢትዮጵያና ሕዝብዋን ሠቆቃ ለማራዘም ብዙ የሠሩትን ደካማዎች ከመጠየፍ ቢያቅባቸው እንኩዋን፥ ልዩ ቀረቤታን እንዳይቸሩዋቸውና የአገር ባለውለታዎችን ጣል ጣል እንዳያደርጉ ሰጋን። ደግመን ደጋግመን የተካድን ሕዝብ ነንና ጥርጣሬያችን መሠረተ ቢስ እሚባል አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትራችን የኤርትራን የልዑካን ቡድን ሲቀበሉና ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር ሲገናኙ፥ ከፊት ቆመው ያየናቸው፥ ጎዶሎ ስብዕና ያላቸው ወንድሞቻችን ይቅርታ ሲደረግላቸው ባንቃወምም፥ የፊት ወንበርን ይዘው ሲገኙ ግን “ታዲያ ለዚህ ድል እንድንበቃ መከራውን የከፈሉት ጀግኖች የት ይቀመጡ?” ብለን ቅናት ቢጤ ወጋን።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፥ ይህ አሁን እርሶ የሚሰብኩትን የአገርና የሕዝብ ፍቅር፥ ይቅርታና አንድነትን ከእርሶ በጣም ቀድሞ ቴዲ አፍሮ ብዙ ብሎበታል። ለኤርትራ አምርሮ አልቅሶዋል። በነፃ አይደለም ዕድሜ  ከፍሎበታል። በጭለማ ቤት ታስሮበታል። ከውጪ አገር እስረኛን ማስፈታት እርሶ ሳያደርጉት በፊት ቴዲ አፍሮ ከሞቃዲሾ በማስፈታት ቀድሞዎታል። ይህን በጎ ተግባር ከቴዲ ተማሩት ለማለት ባልደፍርም፥ መንገዱን ደልድሎ እንደጠበቀዎት ግን እርሶም አይክዱትም። ቴዲ አፍሮ የእርሶና የሚወድዋት አገሮት ባለውለታ ነው። ታዲያ እርሶን ለዚህ ለማብቃት የፈሠሠው የወጣቶች ደም ትኩስ ሆኖ ሳለ “ድንቄም ሰላማዊ ትግል!” ከማለት አልፈው ሙዋቾችን ሲኮንኑ የነበሩ እንዲከቡዎት ለምን ይፈቅዳሉ? ባለውለታዎቻችንን እንድናከብር ብለው ሲናገሩ ነበርና፥ እባክዎ በባለኅሊናዎች ተከበቡ። እነዚህ ዐይን አውጣዎች ለክፉ ቀንና ለቁም ነገር አይሆኑም። ሮጠው እንደመጡ ሮጠው ያመልጣሉ። እርሶ ጥላቻና ቂም በቀልን ተቃወሙ እንጂ፥ ይሉኝታ ቢስነትን ሲሰብኩ አልሰማንም። እነዚህ ይሉኝታ ቢሶች፥ ትናንት የቀን ጅቦችን ሲያንቆለጳጵሱና ጥላ፥ ከለላና መንገድ መሪ ሆነው፥ የሰቆቃውን ዕድሜ ያራዘሙብን ናቸው። ይቀጡ አላልንም! ግን ከሁዋላ ይቀመጡ።

አንድ ሀሳብ አለኝ። አሥመራ ሲሄዱ ቴዲ አፍሮን ብቻ ይዘው ይሂዱ። ከዛም በእርስዎና በኢሳይያስ መካከል ቴዲ ቆሞ፥ ዳህላክ ላይ ልሥራ ቤትን አየዘፈነ በቀኝ እጁ የእርሶን እጅ፥ በግራው የኢሳይያስን አንስቶ ያጨባብጣችሁ። ይህን በማድረግ ትዕይንቱን ኪነታዊ ውበት ያላብሱታል። እርሶም ለሥነ ጥበብ ክፍት ልብ እንዳለዎ ሰምቻለሁ። በዚህ መንገድ የባህል አብዮት ያካሂዳሉ። በዚህ መንገድ ጀግናን ብቻ ሳይሆን ጀግንነትን በኢትዮጵያ እንደገና ይተክሉታል። በዚህ መንገድ ብቻ በኢትዮጵያ ዳግም የቀን ጅቦች እንዳይበቅሉ መንገዱን ይከረችማሉ። የባለፈው የራት ግብዣው ላይ፥ ዳህላክ ላይ ልሥራ ቤት የሚለው ትክክለኛ ዜማ እያለ “ዓለም! ዓለም!” የተባላበት ምክንያት፥ የክቱን ዘፈን አሥመራ ላይ ወይም ዳህላክ ላይ ለማዜም ሆን ብላችሁ ነው የቆጠባችሁት የሚል ቅን ሀሳብ መጣብኝ። ቅን ማሰብ ደግ ነው። እናንተ ከኤርትራ እስክትመለሱ ሌሎቹ በዛኛው ቴዎድሮስ መሪነት ከሩዋጮቹም ጨምሮ፥ ከመሰሎቹ ጋር (ሠለሞን ተካልኝን ሳይዘነጋ) ለሠሩት በደል ንስሀ ገብተው ይጠብቁዎ።

 እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝብዋን ይባርክ! መሪዋንም ይጠብቅ! የሞተላት የሚሞገስበትን ቀንም ያምጣላት!