የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ መብትን ጥሰት በአስቸኳይ እንዲመረመር ጥያቄ ቀረበ

አባይ ሜድያ ዜና

በጅጅጋ የማዕከላዊ እስር ቤት እየተባለ በሚጠራው እስር ቤት ውስጥ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ኢትዮጵያዉያኖች በዚህ የማሰቃያ ቤት ውስጥ ስቃይ እንደሚፈጸምባቸው አንድ የአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች መሥሪያ ቤት  አስታወቀ።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ በአስቸኳይ በዚህ እስር ቤት ውስጥ እየተካሔደ ያለውን ሰቆቃ ከከፍተኛ ኃላፊዎችን ጨምሮ ምርመራ እንዲያደርጉ ይኸው የአለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት አንክሮት ሰጥተው ጠይቀዋል።

የጅጅጋው ማዕከላዊ በመባል የሚታወቀው በአገሪቱ የምስራቅ አካባቢ የሚገኘው ይኸው የማሰቃያ እስር ቤት ዜጎችን በማሰቃየት፤ ሕክምና በመከልከል፤ የሕግ ምክር እንዳያገኙ በመከለከል፤ዘመድ አዝማድ እንዳይጎበኛቸው በማድረግ ከዛም ሲከፋ ምግብ በመከልከል እያሰቃየ ያለ የምድር ሲዖል ማሳያ እንደሆነ ነው ሒዩማን ራይትስ ዋች ባሰባሰበው መረጃ ያሳወቀው።

ከዛ እስር ቤት ውስጥ ታስረው የነበሩ የዐይን ምስክር እንደገለጹት ሰዎች በደረሰባቸው ድብደባ  ምክንያት በእሥር ቤት እንዳሉ ሕይወታቸው ማለፉን በዐይናቸው እንዳዩ ገልፀዋል።

አብዲ ኢሌ በሚል ስም የሚታወቁት በአገሪቷ ሁለተኛ ትልቁ ክልል የሆነውን የምስራቅ ኦጋዴን አካባቢ የሚያስተዳድሩት ፕሬዚደንት አብዲ ሙሐመድ ኡመር በዚሁ እስር ቤት በርካታ ሰቆቃ እያስፈጸሙበት እንደሆነ እና እየፈፀሙበት እንደሆነ የሚያሳዩ የተሰበሰቡት ዶክመንቶች ያሳያሉ።

ምንም እንኳን የክልሉ ቃል አቀባይ ጉዳዩን እንደካዱት ቢገለጽም ዜጎች በዚህ የስቃይ እስር ቤት ውስጥ የአይናችሁ ቀለም አላማረንም ተብለው እንደሚገረፉ ሴቶች የአስገድዶ መድፈር እንደሚፈፀምባቸው በተጨማሪም በእንቅልፍ እንደሚቀጡ 100 ሰዎችን ከዛ ውስጥ 70 ዎቹ ታስረው ሰቆቃው የተፈጸመባቸውን ቃለ መጠይቅ በማድረግ ካሰባሰበው ሪፖርት ማግኘቱን ይፋ አድርጓል።

የክልሉ ቃል አቀባይ አሁንም የሶማሌ ነፃ አውጭውን ጨምረው በርካታ እስረኞችን ፈተናል ብለው ቢሉም ይኸው የልዩ ኃይል ተብሎ በ2008 እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በሟቹ መለስ ዜናዊ የተቋቋመው 40ሺ ልዩ የሚሊሽያ ጦርን በመጠቀም የጦሩም የበላይ ኃላፊ ሆኖ የክልሉ ፕሬዚደንት አብዲ ኢሌ የክልሉን ነዋሪ ለከፋ ሰቆቃ እና ኢሰብዓዊ ድርጊት ሲፈጽሙበት እና እየፈጸሙበት እንዳለ ገልጿል።

በኢትዮጵያ ዜጎችን የማሰቃየት እርኩስ ምግባር በሁሉም አካባቢ እንደሚፈፀም የሚታወቅ ቢሆንም ነገር ግን በሶማሊያ ክልል ግን ያለማቋረጥ እየተካሔደበት ያለ መሆኑን ፍሌክስ ሆርን ለሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶቹ ገልፀዋል።

የሶማሌ ክልልም ከ 1 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በሰላም ማጣት እና በነበረው የእርስ በእርስ ግጭት ተፈናቅሎ እንደነበረም ይታወሳል።