ሞያሌ ዳግም ተረብሻለች ህይወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያንም እንዳሉ ተሰምቷል

አባይ ሚዲያ ዜና

በኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ ዳግም ባገረሸው  ግጭት የአንድ ቀበሌ ሊቀመንበርን ጨምሮ ሌሎች ነዋሪዎችም ህይወታቸውን ማጣታቸው ተነገረ።

የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይሎች በቦታው ጥቃት መክፈታቸውን እየገለጹ የሚገኙ ነዋሪዎች በጥቃቱ የቆሰሉ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ገልጸዋል።

ባሳለፍነው ሃሙስ እንደተጀመረ የተነገረው ይህ ጥቃት ለተከታታይ ቀናት ከባባድ  መሳሪያ ተኩስ በማስተናገድ እንደቆየ ተነግሯል።

የመከላከያ ሰራዊት በቦታው ግጭቱ በተቀሰቀሰበት እለት በአከባቢው እንደነበረ ቢነገርም በሚቀጥለው ቀን ከመሃል እንዲወጣ መደረጉን የሚናገሩ ተገኝተዋል።

በሞያሌ በተቀሰቀሰው ግጭት ህይወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያን ወደ አራት እንደሚደርስ ከአከባቢው የሚወጡ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።

የመከላከያ ሰራዊት ከወራት በፊት በሞያሌ ከተማ በሰላማዊ ኢትዮጵያኖች ላይ በከፈተው ተኩስ በርካታ ህይወታቸውን ሲያጡ በቡዙ ሺህ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ወደ ጎረቤት ኬኒያ መሰደዳቸው ይታወሳል።

በሞያሌ ዳግም በተቀሰቀሰው ግጭት ህይወታቸውን ባጡ ኢትዮጵያውያን የተሰማንን ሃዘን በመግለጽ ለቤተሰቦቻቸው እና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን እንመኛለን።