ብንጀምር ቁንጠጣ (ግርማ ቢረጋ)

ደስታው በዚህ በኩል ፈረሱን ጭኖታል ፣

ፍርሃቱም ነገሰ ይሄን ምን ይሉታል ።

እነዴትስ አድርጌ በየትኛው ልርጋ ፣

 የማይደፈር ነው የሚይዝ ትናጋ ።

እና ምን ሊበጀኝ የትኛውን ልምረጥ ፣

ባያቸው ግዜ እኮ  የነሱን ማሽቃበጥ ።

ድሉ  ተጎስሞ እልልታው ቀጥሎ ፣

የኔ ብቻ ሃሳብ በአይር ተንጠልጥሎ ።

ድሉም  በቀኝ በኩል አጩሎኝ ተመመ ፣

ቀናቶችም ሳይቆይ ባንዳውም ተሾመ ።

ስጋታችን በዛ ሁሉም ተባባሰ ፣

የጎጥ መተሻሸት ጥርስ እያስነከሰ ።

ትንንሽ ቀማኞች ተሰብስበው ገቡ ፣

ጨመረ ከፍ አለ እጅግ ነው ወጀቡ ፣

ታዲያ ዋናዎቹን ምነው ሳተ ክቡ ፣

መቆንጠጥ የለም ወይ በሃብት ከደለቡ ።

ዳግም አየናቸው የጎሪጥ በስሱ ፣

ድሮም ሆኖ ያለው ከአናት መበስበሱ ።

ምንድነው ዝምታው ምንስ ነው አደጋው ፣

ጠራርጎ ለማለፍ ወኔውስ የጠፋው ።

ዝምታው በዛና ቅር ቢለኝ እኔ ፣

አላምንም አልኳቸው እኚህን አረመኔ ።

ታዲያ ከዚህ በላይ ምንስ ነገር ይምጣ

እንዴትስ ልለየው ወይስ ከዳር ልውጣ ፣

በሉኝ ይሄ  ነው ልክ ውዥንብር ሳይመጣ ፣

የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ ፣

ምን ይመስላችኋል  ብንጀምር ቁንጠጣ ? ።

አንፈቅድም እንበለው ይበቃል ጥጋቡ ፣

ምንም እንኳን ቢጓዝ  ጭኗቸው መርከቡ ፣

መሸንቆር መርከቧን አሉ የሚያስቡ ፣

ለሁለተኛውም ዙር ሃገር ሊረከቡ ።

ግንቡን ሊገነቡ ድልድዩን ሊያፈርሱ ፣

ታዲያ ይመቻል ወይ ሁሉን ማግበስበሱ ።

በወገኔ ደም ነው እጁን የታጠበው ፣

ይህ ነው ስጋቴ  እንዴትስ ልመነው ።

የጎሪጥ እይታን ሳልተወው  በሙሉ ፣

ፍቅርን ካባ አድርጌ ወጣሁ ከመርከቡ ።

ለውጡን ለመደገፍ ለመሆንም ጋሻ ፣

ሰብሰብ በል እንግዲህ እንጠንክር ሃበሻ ።

 ጁላይ 2018/ ስቶክሆልም