በዛሬው ዕለት በተለያዩ የማረሚያ ቤቶች ታራሚዎች አመጽ መቀሰቀሳቸው ታዉቋል

በቃሊቲ በደብረ ማርቆስ እና በአርባ ምንጭ እስረኞች አመጽ አንስተው ፖሊስ በተኮሰው ተኩስ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉት እነዚሁ አስረኞች ጉዳት እንደደረሰባቸው ከስፍራው ለመረዳት ተችሏል።

በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የተነሳው ተቃውሞ እስረኞቹ ለኢትዮጵያ ቴሊቪዥን በሰጡት ቃለ መጠይቅ የተነሳ አንዳንድ ፖሊሶች በጉዳዩ ተበሳጭተው እስረኛውን ማሰቃየት በመጀመራቸው የተነሳ እንደሆነ የሚወጡት መረጃዎች ያሳያሉ።

ከዚህ በተጨማሪም በማታው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን  በሽብር ወንጀል ከተከሰሱት ውጭ ክሳቸው እንደማይነሳ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሰጠውን መግለጫ የሰሙ እስረኞች እኛስ ኢትዮጵያዊ አይደለምን? በማለት የተቃውሞ ድምጽ ማሰማታቸውን ተከትሎ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

አንዳንድ ፖሊሶች እስረኞችን በየተራ በማውጣት ከመኻከላቸው የተወሰኑትን መርጠው ከሌሎች እስረኞች በመለየት ወደ አልታወቀ ስፍራም እንደወሰዷቸው  ከስፍራዉ የሚወጡት መረጃዎች ያሳያሉ።

በቂሊንጦ በእስር ቤት ውስጥ የሚተኮሰውን ተኩስ የሰሙ እና መልዕክት የደረሳቸው ቤተሰቦች ወደ ቦታው ያቀኑ ሲሆን የአስለቃሽ ጭስ ወደ ቤተሰቦችም የተተኮሰ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ዜናም የቂሊንጦ እስረኞች የፍርድ ቤት ቀጠሮ ያላቸው ወደ ፍርድ ቤት ላለመሔድ አድማ መምታታቸውም ታዉቋል።

አንዳንድ ፖሊሶች ታራሚዎቹ ለሚዲያ በሰጡት ምስክርነት ቂም ቋጥረው የተለያየ ማስፈራሪያ እና ድብደባ ታራሚዎቹ ላይ ያደርሱባቸው እንደነበር ለቤተሰቦቻቸውና ለሚመለከተው ቢያቀርቡም ሰሚ ባለማግኘታቸው ችግሩ ገፍቶ መጥቶ ዛሬ በጥይት መደብደባቸውን ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ።

ፖሊስ በተኮሰው ጥይት  የቆሰሉ ታራሚዎች   አብዱ አወል፤ ዳዊት ገ/እግዚአብሔር እና ዮናስ ለጋሲ እንደሆኑ ታውቋል። የተመቱትም በወቅቱ ሕክምና ማግኘት አለመቻላቸው ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

ከቃሊቲ በተጨማሪ በደብረ ማርቆስ እና በአርባ ምንጭም እስረኞች አመጽ አንስተው  እንደነበር እና በደብረማርቆስ እና ወልድያ በሚገኙት ማረሚያ ቤት የእሳት አደጋ መነሳቱ  የእሳቱ መነሻም ለጊዜው እንዳልታወቀ ለመረዳት ተችሏል።