“ተገናኙ” (ጌታቸው አበራ)

ከእናት አገር እምዬ ኢትዮጵያ – በማለዳ ታጥቀው ተነስተው፣

በብርሃን ጭለማን ሰንጥቀው – አየር፣ ምድር፣ ባህር አቋርጠው፣

ለዓመታት ጋርዷቸው የኖረውን – የጭለማን ዘመን ግንብ ሊያፈርሱ፣

ረቂቅ ብርሃናዊ ከዋክብቱ – ከወገናቸው አምባ ደረሱ፤

በክቡር “ካፒቴናቸው” ግርማ-ሞገስ – በልበ-ብርሃን እየተመሩ፣

የ’ቲም ለማ’ ልዑካኑ – ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነትን አበሰሩ፤

      በብዙኅን ስደተኞች የመጠለያ ዋርካ፣

      በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ፤

አገልጋይና ተገልጋይ፣ – መሪና ተመሪ ተገናኙ ድንገት፣

በዘመናት ታሪክ – ሆኖ እማያውቅ ክስተት።

 

ተዐምር ነው ሀበሻ!..

ኢትዮጵያውን በልቡ ይዞ – እንደንቦቹ ተመመ፣

ሰንደቁን አውለበለበ፣ – የፍቅር መዝሙሩን አዜመ፤

ኢትዮጵያዊነት ክቡር ነው!..

እናት አገር በዐቢይ ልጆቿን አቀፈች፣

ከልብ ገብቶ በሚሰራጭ – የናፍቆት ፍቅር አጠመቀች።

 

በእረኞቹ ንዝልሃልነት – አገር ጥለው የጠፉትን፣

ከቀዬያቸው፣ ከወንዛቸው፣ – ከበረታቸው የራቁትን፣

እንያን ደማቅ ዕጹብ ፈርጦች፣

ውድ በጎች፣ የዋህ ርግቦች፣ ውብ ጫጩቶች፣

ኢትዮጵያ እጇን ልካ – በዐቢይ እቅፍ መንፈስ አድራ፣

ሰጠቻቸው ህያው ሙቀት – ዳግም ህይወት እሚዘራ፤

 

እንግልት መከራው አከተመ፣

የተቃውሞ ሰልፍ፣ ሃዘን… ቆመ፤

ማዶ-ለማዶ እየተያዩ – መወጋገዝ ተወገደ፣

ወገን-ከወገን በአብሮነት ውል ተጋመደ፤

“ቲማቲምና እንቁላል” ታሪክ ሆኑ፣

የኢትዮጵያ ባለስልጣናትም ጀገኑ፤

 

ተዥጎደጎደለት የሕዝብ አስተያየት – የጥያቄው መዐት፣

ፈሰሱ በቁሙ፣ ያልተጠኑ – መልሶች ከሕዝቡ ፊት ለፊት፤

“ዲሲ” ተደመረች፣ “ኤል ኤን አስከትላ፣

“ሚኒ..” አሰለሰች፣ ዓርማ ተቀብላ፤

አሕዛብ በደስታ ፈካ – የዘመናት ትግሉ ተሳካ፣

(*1) “ደስ በሚል ስቃይ” ተጨነቀ – የደስታ ስሜት እንባ ጨመቀ፣

ሲሳይ፣ በረከቱ ፈሰሰ – ያገረ ልጅ በደስታ ተንፈላሰሰ፤

የኢትዮጵያውያን ቤት-ኤምባሲ – በ’ዲሲ’ ላይ “ተከፈተ”፣

(*2)      “ለካሳም” “ለሽመልስም” – ባዋጅ ጥሪ ተከተተ፤

በጀመሩት ቀና መንገድ – መልካም ተግባር ስለሰሩ፣

አንጸባራቂ ኮከቦቹ – ዐቢይ-ለማ.. ተከበሩ፣

የእማምዬን መዐዛ ሽታ – ባሜሪካን አየር ዘሩ!

ኢትዮጵያዊነት ሞገስ አገኘ፣

ከጽንፍ-አጽናፍ ሰማይ ናኘ!

 

በቁር፣ ሐሩር፣ በበረዶ.. ፣ ለዘመናት ስንጮኽ ያዩ፣

በጭብጨባ፣ በሳቅ-ደስታ – ፊቶቻችን ፈክተው ሲያዩ፣

በ”ምትሃቱ” ተገረሙ – አፋቸውን ከፍተው ቀሩ፣

ከጎናችንም ታደሙ – የኢትዮጵያን ቀን አበሰሩ።

 

ማን አስችሎት በምን አንጀት – ለዚህ ጸጋ አሜክላ..

አሾኽ ሊሆን የሚቃጣ – እንቅፋትን እሚያሰላ?

ማንስ ሊሸሸ ከዚህ ጉዞ – ማን ሊነጠል ከዚህ ድምቀት፣

ከተራራው ጫፍ ላይ ሳይደርስ – ዴሞክራሲን ሳይመሰርት?

ለአንድነት ህይወት ጉዞ፣ ያገር ልጆች ተያያዙ፣

በመደመር አዲስ ቋንቋ – ፍቅር ሰላምን አንግሱ!

 

የድልድዩ መስመር ተዘረጋ – መሪና ሕዝብ ተገናኙ፣

የስልጣኔ ማማ ጫፍ ላይ – አገራቸውን ሳያወጡ ላይተኙ..

ተማማሉ በቀን ብርሃን – ቃል ኪዳናቸውን አሰሙ፣

በሰላም፣ በፍቅር፣ በአንድነት ህብረ-ቀለም ማኅተም አተሙ።

ሐምሌ 26፣ 2010 ዓ/ም

(ኦገስት 1፣ 2018)

====================================================================================

 

*1= ከቴዲ አፍሮ የዘፈን ስንኞች የተዋስኩት ቃል ነው፤

*2= ጠ/ሚ ዐቢይ ከንግግራቸው በአንዱ ወቅት፣ “የኢትዮጵያ ኤምባሲ የካሳም[ካሳ ተ/ብርሃን የወቅቱ የኢትዮጵያ

አምባሳደር]የሽመልስም[በተቃውሞ ላይ የነበረውና ወደ ኤምባሲው ይዘውት የገቡትን ኢትዮጵያዊ] ያሉትን ይመለከታል።