ደምረነ ( ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ )

  እንደመር በሚል መርሆ ኢትዮጵያን በመምራት ላይ ያለው የዶክተር ዓቢይ አህመድ መንግሥት አማካይነት፤  በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል በተፈጸመው እርቅ አምላክን ለማመስገን  ሐምሌ 29 ቀን 2010 ዓ/ ም በዋሸንግተን ዲሲ ለተደረገው ጉባኤ የቀረበ፦  

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ።  

 ሐምሌ 29 2010 ዓ.ም.

አምልኮት ክብር ውዳሴና ስግደት የባህርዩ ለሆነው አንድ አምላክ አብ ወልድ ለመንፈስ ቅዱስ “አብጽሀነ

ለዛቲ ሰአት” እያለን ምስጋና እናቀርባለን።  

ዛሬ በዚህ ቦታ የተሰበሰብነው ያለፍንበትን የመከራ ዘመን እንዴት እንደጀመርነውና እንዳቋረጥነው

በመቃኘት ለአምላካችን ካቀረብነው ምስጋና ቀጥለን፤  በሀገራችንና በቤተ ክርስቲያችን ጉዳይ ሁሉ በሀሳብ በቃል በጽሁፍ በተግባር የተሳተፉትንም ሁሉ እያመሰገን፤ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ስርአት፤  የጠቅላይ ቤተ ክህነት የዜና ቤተ ክርስቲያን ዋና አዘጋጅ በመጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሂ ቅኔ የተደመደመውን ሁሉ ስነ ጽሁፍ ባጭሩ ለመቃኘትም ጭምር ነው።

በሩቅና በቅርብ ሆናችሁ የምትሰሙኝ፦ ብጹአን አባቶች ካህናት አበው ወንድሞቼ ዲያቆናት ምእመናን

ወገኖቼ ዛሬ ይህችን መልእክት ይዥ በፊታችሁ ስቀርብ ደስታየ ፍጽም ነው። 

የዘመናችን ሊቃውንት ይህን የመሳሰሉትን ህዝባውያን ክስተቶች ለመቃኘት የሚያስችሉ Prologue እና Epilogue የሚሏቸው ዘዴዎች አሏቸው። Prologue መሰረታዊ ይዘታቸውን የሚቃኝ ሲሆን። Epilogue መደምደሚያውን የሚቃኝ ነው። 

“ይወድስከ አፈ ነኪር ወአኮ አፈ ዚአከ” እንደተባለው፦ በዚህ ቅኝታችን በቤተ ክርስቲያናችን የተፈጸመውን መነሻ በማድረግ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ታሪከውነትና ያበረከተችውን ሁሉም እየተናገረው ነውና እዚያ ውስጥ አልገባም።  

ዛሬ ከፊታችሁ የቆምኩት ለዚህ ያበቃንን አምላክን በማስቀደም፤ ከቅድስት አገራችን ውጭ ያለነውን 

ሀሳብና ቃል እያፈለቁ  እንድናፈልቅ፤ እየጻፉ እንድንጽፍ፤  ያደረጉንን የአቡጊዳ፤ የኢትዮሚዲያ፤   የቋጠሮ፤ የአባይሚዲያ፤  የዘሀበሻ  የኢካዴፍና የወልቃይት፤  የኢትዮጵያ ሪቪውና የጎልጉ ድረገጾች ባለቤቶች እንኴን ደስ አላችሁ!ለማለት ነው። 

የበጋውን ሀሩር የክረምቱን ቁር ታግሳችሁ በተግባር እየታገላችሁ ከዚህ የደረሳችሁ የዲሲ ዙሪያ ግብረ

ኃይሎች እንኴን ደስ አላችሁ! 

ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ እየዘመራችሁ መንፈሳችንን ስሜታችንን ስታዘመሩን የነበራችሁ የሕሊና

አዘማሪዎች፤  በዘመኑ አገላለጽ አርቲስቶች እንኳ ደስ አላችሁ! የነጻነት ራዲዮ፤ ኢሳት፤ እንዲሁም ያማራ ራዲዮ፦ እንኴን ደስ አላችሁ! እጃችን አብረን ወደፈጣሪ አንስተን በየአደባባዩ  ያለቀስን ሸክ ኻሊድ  ከርሰዎ ጋራ ያላችሁ ሙስሊም ወገኖቻችን እንኳን ደስ አላችሁ!  ይህች ቀን እንድትመጣ በየዘርፉ ተሰልፋችሁ እንዳቅማችሁ የታገላችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ! ከዚህ በመቀጠል ለዛሬው ጉባያችን መነሻ ወደ ሆነን ክስተት በመሻገር የተሰማኝን በጥቂቱ መግለጽ እፈልጋለሁ። 

        ከወያኔ መንግሥት በቀር፦ እስካሁን የነበሩት መንግሥታት የአገርን ሉአላዊነት ባያስደፍሩም፤ ከነሱ በፊት የነበሩትን እየፈነቀሉ መንግስቱን ሲጨብጡ ሀዘን በተቀላቀለው ደስታ ነው። ተልእኴቸውን ፈጽመው በደስታ የተሸኙ መሪወች ግን የሉንም። አሁን እንደመር በሚል መርሆ የተነሱት መሪዎች  የገቡትን ቃል ፈጽመውና ጀመሩትን መልካም ጉዞ ፈጽመው ያገልግሎት ዘመናቸውን አጠናቀው ለተተኪው ሲያሻግሩ እንኴን ደስ አለዎ በመባል በደስታ በሀሴት ለመሸኘት እንዲበቁ እንድንጸልይላቸው አሳስባለሁ። 

ይህን ካልኩ በኌላ ዶክተር ዓቢይ ይዘው ብቅ ስላሉት ስለ መደመር ጥቂት የምለው አለኝ። ከዚህ ቀደም

ተደጋግሞ እንደተገለጸው  [ሙሉውን አንብበው ለመረዳት ከፈለጉ ደመራ ] ወይም መደመር ለክፉ ቀን ደጀን መከላክያ፤ ለደግ ቀን ደግሞ ለደስታ ለፍስሀ ለሳቅ ለፈገግታ እንዲያገለግሉን ሊቃውንት አባቶቻችን ከዘረጉልን ቅርሶች አንዱ ነው።  ለዘረጉልን ለቀደሙ ሊቃውንት አበው ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል።  

እንደሚታወቀው ለ27 ዓመታት በጥፋት የመራን የወያኔ መንግሥት ኢትዮጵያ የምትባለውን ስነ

ህሊናችንን  (nervous system) ከሁለንተናችን እንድትደመሰስ ያለውን ሁሉ ኃይል ተጠቅሞ ነበር።

የተከበሩ አቶ ለማ መገርሳ “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” የምትለው አጭር አረፍተ ነገር ካንደበታቸው

ከፈለቀችበት ቅጽበት ጀምሮ የህሊናችን ሞተር (nervous system) ኢትዮጵያዊነታችን እንደገና አቀጠቀጠ።  ዶክተር ዓቢይ ቀጠሉና “ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ እንሆናለን” እያሉ ብቅ ሲሉ ኢትዮጵያዊነትን ከጊዜ በኋላ ከሚለመድ ሱስነት ወደ ሁለንታዊነት በስፋት ወነጨፉት

ለኛ በተለይ ባብነቱ ትምህርት (ቅኔ) ቤት ላደግን ሰወች ኢትዮጵያ በደማችን ውስጥ ያለች የህሊና

ብልጭታ (synapses firing) ናት። ዶ ክተር ዓቢይ አህመድ እንደመር እያሉ ብቅ ሲሉ በኢትዮጵያ ምድርና በውጭ የተበተነው ኢትዮጵያዊ ትውልድ ተገናኘ። በቋንቋና በክልል ተለያይቶ በነበረው ህብረተ ሰብ ሰውነት ኢትዮጵያዊነታችን ማቀጥቀጥ ጀመረች። ከሱስነት ወደ እሳታዊት ደመራነት ተሻገረች። እየበራች ቦግ እያለች መጣች። ኢትዮጵያን ሲያበጇት ሲያቆነጇት ሲሞቱላት ከነበሩት ሊቃውንት ጋራም ተደመርን። 

ኢትዮጵያን ሲያበጇት ሲያቆነጇት የነበሩትን የኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አበውን ኢትዮጵያዊነት ስነ

ልቡና ለመረዳት፤ ከዚህ ቀደም በታሪካችን በሃይማኖታችን በባህላችን ደጋግመን ስለደመራ ካነበብነው ሁለት ጥቅሶች ብቻ እጠቅሳለሁ። 

“ዕቀብ ኩልነ ዘእንበለ ጻእብ፤ወዘእንበለ ተመውዖ፤ ወዘእንበለ ማዕቀፍ።አድኅን አእጋሪነ እምዳህጽ፤ ወአዕይቲነ እም አንብእ፤  ወነፍስተነ እሞተ ኃጢአት። ወደምረነ ምስለ እለ ይድህኑ ብከ በጸሎተ ኩሎሙ እለአስመሩከ” (ሊጦን ዘሰርክ)።  

ያለ ጸብ፤ ያለ መሸነፍ፤ ያለ እንቅፋት፤ እግሮቻችንን ከዳጥ፤ አይኖቻችንን ከእንባ ፤ነፍስና ስጋችንን በሰው

ህሊና ትዝብት ውስጥ ገብተን ተመዝነን ቀለን ከመገኘት ጠብቀን። በቀና መንፈስ “ፍትህ ጎደለ ደሀ ተበደለ” እያሉ ባንደበታቸውና በተግባራቸው ካገለገሉህ ቅዱሳን አባቶች ጋራ ደምረን።  

ሁለተኛይቱ ጥቅስ፦“ወከመ አስተጋባእካ ለዛቲ ብስት እንተ ዝሩት ይእቲ በአድባር በገዳም ወበቆላት

ከማሁ ኪያነሂ አስተጋብአነ  በመለኮትክ እምኩሉ ህሊና እኩይ ወውስተ ሃይማኖት ፍጽምት” (ጎርጎርዮስ ገጽ

373 ቁ 27-28)እያልን በቅዳሴ የምናቀርባት ናት።

ማለትም፦ በተለያዩ ቦታዎች ተዘርተው በቅለው አሽተው አፍርተው ተወቅተው ተፈጭተው በውሀ

ተለውሰው ወደ ዚህች ህብስትነት እንደ ደመርካቸው፤ በተለያዩ ዓለማት አህጉራት መካናት መንደሮች ቀበሌዎች የተበተነውን በተለያዩ ቋንቋዎች ባህሎች እምነቶች የሚኖረውን ደቂቀ አዳምበህብረት በሰላም በፍቅር ለውሰህ ደምረን

ይህች ህብስት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን ባንድምታው ግንዛቤ፤  ክርስቶስ

ከቅድስት ድንግል ማርያም ከነሳት ሰባዊነት በኩል በዓለም ካለው ከደቂቀ አዳም ጋራ ትደምረናለች። ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው በዜግነት በሥጋ በቌንቋ በባህልና በመልክአ ምድር ኢትዮጵያዊነታችን ከምታስተሳስረን ወገኖቻችን  ጋራ ትደምረናለች።ይልቁንም ከዚህ ሁሉ በራቀና በረቀቀ እምነት “ዘነስአ እምግዝእተ ኩልነ” እያሉ ነፍስ የተለየው መለኮት የተወሀደው ነው ብለው እየመሰከሩ ከሚቆርቡት ከኦሬንታል ክርስቲያኖች ጋራ ትደምረናለች። ይላሉ ሊቃውንት አባቶች። [ደመራ የጸሎት ስርአት ወይስ አርበኝነት በሚል ርእስ ያቀረብኩትን ይመልከቱ።]  

ከዚህም ጋራ፤ ጠቅላይ ምኒስትሩ ወደ ዚህ ተልእኮ ከመምጣታቸው በፊት ባንድ ወቅት ባንድ መድረክ ላይ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ስነ ልቡና ተቀርጸው ስላደጉ ኢትዮጵያውያን የሰጡትን ምስክርነት ማውሳት እወዳለሁ። “ከዚህ በፊት ልጆች ዳዊት እየደገሙ ያድጋሉ። በኋላም ያንኑ እያወጉ አካባቢውን ያገለግሉ ነበር። የአሁኖች ግን ሳንቲም መለቃቀም ይመስለኛ” ይህ አባባላቸው ለእኔ እና ለሚመስሉኝ ያስተላለፉት መልእክት እንደሆነ ተሰማኝ። የሌላውን አላውቅም።  በዚህ ዘመን ሳንቲም ከመለቃቀም ተላቅቄ፤ እንደ ድሮዎቹ ሆኜ ባለመገኘቴ በራሴ እንድፈርድ እራሴን እንድታዘብ አድርጎኛል። የህሊና ጅራፍ ሆኖ 

ዶክተር ዓቢይ “ እናንት የሃይማኖት ሰዎች ድህ ተበደለ ፍርድ ጎደለ በሉ” ያሉትን ክቡር ፕሬዝደንት

ዶክተር ሙላቱ ተሾመም ደገሙት። የሁለቱ ተመሳሳይ ንግግር ሚያሳየው ክርስቶስ ሞትን አሸንፎ ከተነሳ በኋላ “ተውህበኒ ስልጣን በሰማይ ወበምድር” ብሎ “ሂዱ እስከ ምድር ዳርቻ አስተምሩ” እያለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኛ ለካህናት የሰጠንን ስልጣን በአጽንኦ የሚያሳስብና የሚያስገነዝብ ነው። ይህም ማለት እኛ ካህናት በሞራል በእምነት በንጽህና በእውቅትና በጥበብ ከፖለቲካ ሰዎች ልቀን መታየት አለብን ማለት ነው። ይህንንም አልሆንኩም። 

”እናንተ ኦርቶዶክሶች ብዙ ነገር አሏችሁ። ከነዚያም ውስጥ የጋራችን የሆነው የደመራው በዓልና የጥምቀቱ በዓል ናቸውና አታበላሹብን“ ብለው የተማጸኑላቸውም፤ ሊቃውንት አበው እንዳስተማሩን የደመራው በዐልና የጥምቀቱ በአል ይዘት ስርአተ ሰማይንና ስርአተ ምድርን የሚያሳዩ እንደ ሥጋና ነፍስ የተዛመዱ ተፈጻጻሚዎች ናቸው። 

በስርአተ ምድር ይዘታቸው አገር በቀል የሆኑትን ደሀ የሚበድሉት የፖለቲካ መሪዎች፤ ፍርደ ገምድል

የሆኑትን ዳኞ እንድንገስጽበት፤ በክርስቶስ ጸድቀናል  እያሉ ከውጫ የሚመጡትን ወራሪዎችንም ክርስቶስ ያወጃትን ጽድቅ ልታውቁ ይቅርና ከኦሪቱ ያልደረሳችሁ አህዛቦች ናችሁ እያለን በመደመር ኢትዮጵያን እንድንጠብቅበት የወረስነው መከላካያች ነበር። ይህንንም ውርስ ጠብቄ አልተገኝሁም።

በስርአተ ሰማይ ይዘታቸው ደግሞ በሰባዊነታችን ክርስቶስ ከለበሰው ሰባዊነት ጋራ በመዋሀድ፤ በጥምቀቱ

ያወጃትን ጽድቅ በመልበስ ህሊናችንን ከሚዋጋው ረቂቅ ፈታኝ መንፈስ ተዋግተን  የምናሸነፍበት ነበር። ይህም አልሆነም። 

ባቋረጥነው በ27ቱ ዘመነ- መንሱት ቅድስት ቤተ ክርስቲያኔ ያስተማረችኝንና የሰጠችኝን አደራ

ያልተወጣሁትን፤  በጣቴ ልነካው የፈራሁትን፤ ባንደበቴ ልመሰክረው የሸሸሁትን ሁሉ፤ እየፈጸሙ በሞት ያለፉት ዜጎች መንፈሳቸው ስለሚወቅሰኝ እጨነቃለሁ። ከሞት በተረፉት ሕያዋን ሰማእታት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ፊት ስቆም ደግሞ እጅግ አፍራለሁ። በዚህ ሁሉ ስሜቴ ደፍሬ ዛሬ በዚህ አደባባይ በፊታችሁ ስቆም ይቅርታ እጠይቃለሁ። 

የሊቃውንቱ ቅርስ የሆኑት መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል  በሊቃውንቱ የምስክር መግለጫ ቅኔ

አፈጻጸሙ ከምንም የማይገናኝ መሆኑን በበዐሉ አውድ ላይ የሰጡት ታሪካዊ ምስክርነት እንዳለ ሆኖ፤ እርቁ እንዲከናወን የጣሩ ልኡካንና እርቁን ያከናወኑት አባቶች ከዋሸንግተን ዲሲ ሲለቁ፤ “ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ከመንበሩ ከተወገዱበት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን የገቡ ብዙ ስህተቶች እንዳሉ ግልጽ ነው። ሆኖም በሊቃውንቱ ተጠንተውና ተመርምረው፡ በሲኖዶስ ጸድቆ በሚወጣው መመሪያ ስለሚስተካከል፤ ከመደመር በቀር እስካሁን የታዩ ትን ስህተቶች እያነሳችሁ ከመጠቋቆም ታገሱ ሲሉ በግልም በማህበርም የሰጡንን አደራ የመጠበቅ ሀላፊነት እንዳለብኝ አምናለሁ።  

በዚህ አጋጣሚ በውጭ ላለን ለአበው ካህናት ለአኀው ዲያቆናት ለጠቅላላው ምእመናን የማሳስበው፤

የሰጡንን አደራ በመጠበቅ ከዚህ ቀደም በተከሰቱት ስህተቶችም ሆነ አዳዲስ ነገር በመፍጠር በመጠቋቆም ምእመናን ግራ ከማጋባት መቆጠብ አለብን። ይልቁንም በእርግጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ከሆንና ሀላፊነትም ከተሰማን፤ ጠንካራና አድር ባይ ያልሆነ፤ በመከራ የተፈተነ፤  በፈተናው ዘመን የገቡትን ስህተቶች እያረመ እየገሰጸ የሚታገል የሊቃውንት ጉባዔ እንዲመሰረት በአካባቢያችን ካሉት ከኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ካህናትና ከመላ ህዝበ ክርስቲያኑ ጋራ ተደምረን  መታገል እንዳለብን ማሳሰብ እወዳለሁ። 

በተረፈ በሊጦኑ ጸሎታችን ሀሳቤን እደመድማለሁ። “ዕቀብ ኩልነ ዘእንበለ ጻእብ፤  ወዘእንበለ ተመውዖ፤

ወዘእንበለ ማዕቀፍ።  አድኅን አእጋሪነ እምዳህጽ፤ ወአዕይቲነ እም አንብእ፤  ወነፍስተነ እሞተ ኃጢአት።  ወደምረነ ምስለ እለ ይድህኑ  ብከ በጸሎተ ኩሎሙ እለአስመሩከ” (ሊጦን ዘሰርክ)። 

አምላካችን ሆይ! መጀመሪያ ሁላችንንም ከጸብ ጠብቀን። በመካከላችን ጸብ ከተከሰተ በምንሸነፍበት

በስህተት መስመር ከመሰለፍ ጠብቀን። እግረ ህሊናችንን ከሞራል ውድቀት ዳጥ፤ ዓይኖቻችንንም ከጸጸት እንባ፤ ነፍስና ሥጋችንን በሰው ህሊና ትዝብት ውስጥ ገብተን ተመዝነን ቀለን በመገኘት ከመሸማቀቅ ጠብቀን። ከወደቁበት ስህተት ተጸጽተው ለመመለስ ባህርይ ከሌላቸው ሰዎች ጋራ ከመደመርም አድነን። ተጣሉ የሚሉ መሪወች  መልሰህ  አታምጣብን። በቀና መንፈስ ፍትህ ጎደለ ደሀ ተበደለ እያሉ ባንደበታቸውና በተግባራቸው እያገለገሉ ካለፉት ቅዱሳን አባቶች ጋራ ደምረን እያልን እንጸልይ። ይህን ጸሎት ወደ ተግባር ለመለወጥም፤ አምልኮት ክብር ውዳሴና ስግደት የባህርዩ የሆነው አብ ወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ይርዳን። 

ሌሎች ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ጦማሮች የሚከተለዉን ድረገጽ ይመልከቱ::

http://www.medhanialemeotcks.org/